Skip to main content
Surveillance
Self-Defense

ከማክኦኤስ ላይ ውሂብዎን ደኅንነቱ በተጠበቀ መንገድ መሰረዝ

Last Reviewed: July 20, 2018

This page was translated from English. The English version may be more up-to-date.

ማስታወሻ:- ዘመናዊ የማክኦኤስ ስሪቶች ጠቅላላ ድራይቭዎን ለማመስጠር ፋይልቯልት2ን እንዲጠቀሙ ይጠቁማሉ፡፡ ውሂብዎን ለመጠበቅ ይህንን እርምጃ እንዲወስዱ እንመክራለን፡፡ ጠቅላላ ድራይቭዎን ካመሰጠሩ ውሂብዎን ደኅንነቱ በተጠበቀ መልኩ ስለመሰረዝ መጨነቅ አይኖርብዎትም፡፡ ምክንያቱም ዋና የምስጠራ ቁልፍ እርስዎ በሚቆጣጠሩት የይለፍ ቃል ስለሚጠበቅና በድራይቩ ላይ ያለው ውሂብ እንዳይመለስ ሲፈልጉ መቀየር እና ማጥፋት ስለሚችሉ ነው፡፡ ስለ ፋይልቯልት2 ምስጠራ የበለጠ መረጃ ይገኛል፡፡

ከታች ያሉት መመሪያዎች ውሂብ ከ ተሽከርካሪ ድራይቮች ላይ ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ እንዲወገድ ለማድረግ ብቻ ያገለግላሉ። እነዚህ መመሪያዎች የሚያገለግሉት ለቀድሞዎቹ ዲስክ ድራይቮች እንጂ በዘመናዊ ኮምፒተሮች፣ የዩኤስቢ ቁልፎች / የዩኤስቢ ተምብ ድራይቮች ወይም የኤስዲ ካርዶች / ፍላሽ ሚሞሪ ካርዶች ውስጥ በመደበኛነት የምናገኛቸው ሶሊድ ስቴት ድራይቮች(SSDs) አይደለም። በ ኤስኤስዲዎችን፣ የዩኤስቢ ፍላሽ ድራይቮች እና ኤስዲ ካርዶችን ደኅንነቱ በተጠበቀ መንገድ መሰረዝ በጣም ከባድ ነው! ይህ የሆነበት ምክንያት እነዚህ የድራይቭ አይነቶች ዊር ሌቭሊንግ የሚባል ዘዴን በመጠቀማቸው እና በውስጣው የያዙትን የመረጃ አሀዶች በዝቅተኛ ደረጃ ፍለጋ ስለማይሰጡ ነው። (ይህ ደኅንነቱ የተጠበቀ መሰረዝ ላይ እንዴት ችግር እንደሚያስከትል የበለጠ ለመረዳት እዚህማንበብ ይችላሉ።) ኤስኤስዲ ወይም ዩኤስቢ ፍላሽ ድራይቭ የሚጠቀሙ ከሆነ ከዚህ በታች ወዳለው ክፍልይዝለሉ።

ኮምፒውተርዎ ውስጥ የቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ውስጥ ሰነድ ሲያስገቡ እና ቅርጫቱን ባዶ ሲያረጉበት ሰነዱ ሙሉ በሙሉ አለመጥፋቱን ያውቃሉ? ኮምፒውተሮች በመደበኝነት ሰነዶችን "አይሰረዙም"። አንድ ፋይል ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ሲያስገቡ ኮምፒውተርዎ ሰነዱን እንዳይታይ ያደርግና እና ፋይሉ የተጠራቀመበትን የዲስክ ክፍል ወደፊት ሌላ ሰነድ እንዲጻፍበት ክፍት ያደርገዋል:: ይህም አዲስ ውሂብ ከመጻፉ በፊት ሳምንታት፣ ወራት ወይም አመታት ሊወስድ ይችላል። ይህ እስኪሆን ድረስ ”የተሰረዘው“ ሰነድ ለተለመደው ተግባር እንዳይታይ ሆኖ በዲስኮዎት ላይ ይቆያል። እናም በትንሽ ድካም እና በትክክለኛ መሳሪያ (እንደ “አንዲሊት” ሶፍትዌር ወይም ፎርንሲክ ያሉ ዘዴዎች) “የተሰረዘውን” ፋይል መልሶ ማውጣት ይችላሉ።

ሰነድን ለዘላለም ለመሰረዝ ምርጡ መንገድ ወዲያውኑ በሌላ ነገር መተካቱን ማረጋገጥ ነው። ይህም መጀመሪያ ተጽፎ የነበረውን ሰነድ መልሶ ማውጣትን አዳጋች ያደርገዋል። ስርአተ ክወናዎ ለእርስዎ ይህንን ማድረግ የሚችል ሶፍትዌር ሊኖረው ይችላል። ይህ ሶፍትዌር በኮምፒውተርዎ ዲስክ ላይ ያለውን “ባዶ” ቦታ በሌሎች ትርጉም አልባ በሆኑ ውሂቦች ይተካል፤ በዚህም የተነሳ የተሰረዘው ውሂብ ሚስጥራዊነት ይጠብቃል።

ደኅንነቱ የተጠበቀ ስረዛ በማክኦኤስ anchor link

ከኦኤስ ኤክስ 10.4 እስከ 10.10 ሰነዱን ወደ ቅርጫት በማንቀሳቀስ እና Finder > Secure Empty Trash የሚለውን በመምረጥ ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ መሰረዝ ይችላሉ፡፡

ደኅንነቱ የተጠበቀው ቅርጫቱን ባዶ የማድረግ አገልግሎት ከሞዴል ኦኤስ ኤክስ 10.11 በኋላ ተወግዷል፡፡ ምክንያቱም አፕል አብዛኛዎቹ ዘመናዊው ሞዴሎች በሚጠቀሙበት ፋስት ፋላሽ(SSD) ላይ ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ መሰረዝ እንደሚችል ዋስትና መስጠት ስላልቻለ ነው፡፡

በድሮው ሀርድ ድራይቭ በኦኤስ ኤክስ 10.11 የሚጠቀሙ ከሆነ እና በኮማድላይን መጠቀም ምቾት የሚሰማዎት ከሆነ የማክን ሰነዶች ላይ ደርቦ ለመጻፍ ትዕዛዝ srm መጠቀም ይችላሉ፡፡ ሙሉ መመሪያዎች (በእንግሊዝኛ) እዚህ ይገኛሉ፡፡

ምንም እንኳን ኦኤስ 10.12 ላይ የተወገደ ቢሆንም ኮዱን አሁንምsrm መጫን ይቻላል፡፡

ስለ ደኅንነቱ የተጠበቀ መሰረዣ መሳሪያዎች ገደቦች ማስጠንቀቂያ anchor link

ከላይ ያለው ምክር በሚጠቀሙበት ኮምፒዩተር ዲስክ ላይ ሰነዶችን ብቻ ይሰርዛል። ከላይ ያሉት ማናቸውም መሳሪያዎች በኮምፒተርዎ፣ በሌላ ዲስክ ወይም የዩኤስቢ ድራይቭ፣ "Time Machine"፣ በኢሜይል ሰርቨር፣ በደመና ውስጥ ወይም ወደ እውቅያዎችዎ የተላኩትን የመጠባበቂያ ቅጂዎችን አይሰርዙም። አንድን ፋይል በአስተማማኝ ሁኔታ ለመሰረዝ፣ ያጠራቀመበት ወይም የተላከበትን ሁሉም ቦታ ቅጂዎችን ማጥፋት አለብን። በተጨማሪም አንድ ፋይል በደመናው ውስጥ ከተከማቸ (ለምሳሌ:- በ ድሮፕቦክስ ወይም በሌላ ሰነድ ማጋሪያ አገልግሎት አማካኝነት) ለዘላለም የሚጠፋበት መንገድ የለም።

እንደአለመታደል ሆኖ ሌሎች ደኅንነቱ የተጠበቀ መሰረዣ መሳሪያዎች ሌሎች ገደቦች አሉባቸው። ከላይ የተሰጠውን ምክር ቢከተሉ እና ሁሉንም የሰነድ ቅጂዎችን ቢደመስሱ እንኳ የተደመሰሱ ሰነዶች ጥቂት ዱካ በኮምፒውተራችን ላይ ሊቆዩ የሚችሉበት እድል አለ። ሰነዶቹ በትክክል ስላልተደመሰሱ ሳይሆን የተወሰኑ የስርዓተ ክወና ክፍሎች ወይም ሌሎች መተግበሪያዎች ሆን ተብሎ የተመዘገቡበትን መዝገብ ይይዛሉ።

ይህ ሊመጣ የሚቻልባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። ነገር ግን ሁለት ምሳሌዎችን ማንሳት ሊሆን የሚችልበት ዕድሎች እንዳሉ ለማሳየት በቂ ናቸው። በዊንዶውስ ወይም ማክኦኤስ፣ ማይክሮሶፍት ኦፊስ በ"የቅርብ ጊዜ ሰነዶች" ምናሌ ውስጥ ሰነዱ ቢሰረዝም(አንዳንድ ጊዜ ኦፊስ የይዘት ፋይሎችን የያዘ ጊዜያዊ ቅጂም ሊያስቀምጥ ይችላል) የሰነድ ስም ሊያኖሩ ይችላሉ። ሊብሬኦፊስ እንደ ማይክሮሶፍት ኦፊስ ብዙ መዝገቦችን ሊይዝ ይችላል። እናም ምንም እንኳን ፋይሉ በአስተማማኝ ሁኔታ ቢሰረዝም የተጠቃሚው ዝርዝር የሰነድ ታሪክ የሰነዱን ስም ያካተተ ትዕዛዞችን የያዘ ሊሆን ይችላል። በተግባር ግን እንደዚህ አይነት ባህሪ ያላቸው በደርዘን የሚቆጠሩ ፕሮግራሞች ሊኖሩ ይችላሉ።

ለዚህ ችግር እንዴት ምላሽ መስጠት እንደሚቻል ማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። አንድ ሰነድ ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ከተሰረዘ በኋላ እንኳን ስሙ ለተወሰነ ጊዜ በኮምፒውተሩ ላይ ይኖራል። ስሙ በሙሉ ጠፍቶ እንደሆነ 100% እርግጠኛ ለመሆን ብቻ ዲስኩን በሙሉ እንደገና መጻፍ ብቸኛው መንገድ ነው። አንዳንዶቻችሁ "መረጃው የትኛውም ቅጂ ወደ የትኛውም ቦታ መኖሩን ለማየት ዲስኩ ላይ ጥሬ ውሂብ መፈለግ እችላለኹ?" ብለው ይጠይቁ ይሆናል። መልሱ አዎን እና አይደለም የሚል ነው። ዲስኩን መበርበር ውሂቡ በዲስክ ውስጥ የሚገኝ እንደሆነ ይነግርዎ ይሆናል። ነገር ግን አንዳንድ ፕሮግራሞች የተጨመቁ ወይም በሌላ መንገድ የተጣቀሱ ማጣቀሻዎች ካሉ አይነግርዎትም። በተጨማሪም ፍለጋው ራሱ አሻራ እንዳይተው ይጠንቀቁ! የፋይሉ ይዘቶች ሊገኙ የሚችሉበት ዕድል ዝቅተኛ ቢሆንም ግን የማይሆን አይደለም። ሙሉውን ዲስክ መገልበጥ እና አዲስ ስርዓተ ክወና መጫን ሰነዱ እንደ ተሰረዘ 100% እርግጠኛ ለመሆን ብቸኛው መንገድ ነው።

ያረጀ ሃርድዌር ማስወገድ ሲያስፈልግ የሚደረግ ደኅንነቱ የተጠበቀ ስረዛ anchor link

አንድ የሃርድዌርን መጣል ወይም በኢቤይ ላይ ለመሸጥ የሚፈልጉ ከሆነ ማንም ሰው የእርስዎን ውሂብ ማውጣት አለመቻሉን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ። ጥናቶች እንደሚያሳዩት የኮምፒውተር ባለቤቶች ብዙውን ጊዜ እንዲህ ማድረግ አይሳካላቸውም። ሃርድ ድራይቮች ብዙ ጊዜ ከፍተኛ ሚስጥራዊ የሆኑ መረጃዎችን እንደያዙ ነው እንደገና የሚሸጡት። ስለዚህ ኮምፒውተር ከመሸጥ ወይም እንደገና ጥቅም ላይ ከመዋልዎ በፊት በመጀመሪያ, በውስጡ ያለውን የመረጃ ማጠራቀሚያ በማይረባ ነገር መተካትዎን ያረጋግጡ። ምንም እንኳን ወዲያውኑ ባያስወግዱት ህይወቱ ያበቃ ኮምፒውተር ካለዎትና ከአሁን በኋላ ጥቅም ላይ የማይውል ከሆነ አንድ ጥግ ላይ ወይም ቁም ሳጥን ውስጥ ከማስቀመጥዎ በፊት ሃርድ ድራይቩን ማጽዳት የበለጠ አስተማማኝ ይሆናል። ‘ድሪክስ ቡት ነደ ኑክ’ ለዚህ ዓላማ የተሰራ መሣሪያ ሲሆን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል የሚያሳዩ በርካታ መልመጃዎች ( ይህንን ጨምሮ) በመላው ድር ይገኛሉ።

አንዳንድ ሙሉ ዲስክ ምስጠራ ሶፍትዌሮች የመደበኛ ቁልፉን የማጥፋት ችሎታ አላቸው። በመሆኑም የተመሰጠሩ የሃርድ ድራይቭ ይዘቶችን መገልበጥ ፈጽሞ አይቻልም። ቁልፉ ትንሽ መጠን ያለው መረጃ በመሆኑ እና በፍጥነት ሊጠፋ በመቻሉ እንደ ድሪክስ ቡት ነደ ኑክ ካሉ ሶፍትዌሮች ጋር ለትልቅ ድራይቮች በጣም ብዙ ጊዜ ሊወስድ የሚችለውን እንደገና ለመጻፍ በጣም ፈጣን አማራጭ ነው። ሆኖም ግን ይህ አማራጭ ተገቢ የሚሆነው ሃርድ ድራይቮ ሁልጊዜ የሚመሰጠር ከሆነ ነው። ሙሉ ዲስክ ምስጠራን ቀድመው የማይጠቀሙ ከሆነ ከማስወገድዎ በፊት ሙሉውን ዲስክን እንደገና መጻፍ ያስፈልግዎታል።

ሲዲ ወይም ዲቪዲ-ሮምስ ማስወገድ anchor link

ሲዲ ወይም ዲቪዲ-ሮም ወደማስወገድ ጋር ስንመጣ ወረቀት ሲያስወግዱ እንደሚያደርጉ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ አለብዎ። ብዙ ገንዘብ የማያባክኑ ማስወገጃዎች አሉ። ምንም ስሱ መረጃዎች አለመያዛቸውን ፍጹም እርግጠኛ ካልሆኑ በስተቀር ሲዲ ወይም ዲቪዲ-ሮምን ወደ ቆሻሻ ቅርጫት አይወርውሩ።

ሶሊድ ስቴት ዲስኮችን(SSDs)፣ ዩኤስቢ ፍላሽ ድራይቮችን እና ኤስዲ ካርዶችን ደኅንነቱ በተጠበቀ መንገድ መሰረዝ anchor link

እንደ አለመታደል ሆኖ በአሰራር ስልታቸው ምክንያት ሶሊድ ስቴት ዲስኮችን(SSDs)፣ ዩኤስቢ ፍላሽ ድራይቮችን እና ኤስዲ ካርዶች ውስጥ ያሉ ሰነዶችን ወይም ባዶ ቦታዎችን ለመሰረዝ አይቻልም ለማለት ቢከበድ እንኳን አስቸጋሪ ነው። በዚህ ምክንያት ራስዎን ከመጠበቅ አንፃር እጅግ የተሻለው አማራጭ ምስጠራ ነው። እንዲህ ካደረጉ በኋላ ሰነዱን በዲስክ ውስጥ ማንኛውም ሰው ቢያገኘው እንኳን የሚመለከተው እንደ የማይረባ ነገር ነው፡፡ እናም ምስጠራውን እንዲፈቱ ሊያስገድድዎት አይችልም። በአሁን ሰዓት ከኤስኤስዲ ላይ መረጃዎን የሚያስወግድ ጥሩ የሚባል አጠቃላይ ቀደም ተከተል ማቅረብ አንችልም። ለምን ውሂብ መሰረዝ በጣም ከባድ እንደሆነ ማወቅ ከፈለጉ ንባብዎን ይቀጥሉ።

ቀደም ብለን እንደጠቀስነው ኤስኤስዲ እና የዩኤስቢ ፍላሽ ድራይቮች ዊር ሌቭሊንግ የተባለ ስልት ይጠቀማሉ። ዊር ሌቭሊንግ በከፍተኛ ደረጃ የሚሰራው እንደሚከተለው ነው። በመጽሐፍ ውስጥ እንዳሉ ገጾች በዲስክ ውስጥ ያለው በእያንዳንዱ ቦታ በብሎኮች የተከፈለ ነው። አንድ ሰነድ በዲስክ ላይ ሲጻፍ የተወሰነ ብሎክ ወይም ብሎኮች(ገጾች) ይይዛል። ሰነዱን ለመተካት ከፈለጉ ማድረግ ያለብዎት ለዲስኩ በብሎኮች ላይ እንደገና እንዲጽፍ መንገር ነው። ነገር ግን በኤስኤስዲ እና የዩኤስቢ ፍላሽ ድራይቮች በመሰረዝ እና እንደገና መጻፍ ብሎኩን ከጥቅም ውጭ ሊያደርገው ይችላል። ማገልገል የማይችል እስኪሆን ድረስ እያንዳንዱ ብሎክ በማጥፋት እና እንደገና መጻፍ ሊያገለግል የሚችልበት መጠን የተገደበ ነው።(ልክ በአንድ የወረቀት ገጽ ላይ ደጋግመው በእርሳስ እየጻፉ ቢያጠፉ ወረቀቱ እንደሚቀደድ ወይም ከጥቅም ውጭ እንደሚሆነው ማለት ነው።) ይህን ለመመከት ኤስኤስዲ እና የዩኤስቢ ፍላሽ ድራይቮች እያንዳንዱ ብሎክ ላይ የሚጻፈው እና የሚጠፋው ብዛት ተመሳሳይ መሆኑን ለማረጋገጥ ይሞክራሉ፤ በዚህም ድራይቩ በተቻለ መጠን ለረዥም ጊዜ ይቆያል። ይህ ሂደት ነው ዊር ሌቭሊንግ የሚባለው። እንደ የጎንዮሽ ጉዳት አንዳንድ ጊዜ ሰነዱ በመጀመሪያ የተቀመጠበትን ብሎክ በማጥፋት እና እንደገና በመጻፍ ፋንታ ያንን ብሎክ በመተው ወይም የማይሰራ የሚል ምልክት በመተው የተቄረውን ሰነድ በተለየ ብሎክ ያስቀምጣል። ይህ በመጽሐፉ ውስጥ ገጹን ሳይለውጥ የተሻሻለውን ፋይል በመጻፍ እና በሌላ የመዝገበ-ቃሉ ማውጫ ላይ ወደ አዲሱ ገፅ እንደገና መጻፍ ማለት ነው። ይህ ሁሉ የሚሆነው በዲስክ ኤሌክትሮኒክስ ውስጥ በጣም ዝቅተኛ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚከሰተው። ስለዚህ ስርዓተ ክወናው ምን እንደፈጠረ እንኳን አያውቅም። ይሄ ማለት አንድ ሰነድ ላይ ደርቦ ለመጻፍ ቢሞክር እንኳ ድራይቮ በትክክል ደርቦ እንደገና ለመጻፉ ምንም ዋስትና የለም። ለዚህም ነው የኤስኤስዲዎችን ደኅንነቱ በተጠበቀ መንገድ መሰረዝ ይህን ያህል ከባድ የሆነው።