Skip to main content
Surveillance
Self-Defense

ከስለላ ራስን መጠበቅ

ይህ መመሪያ ለማን ነው? anchor link

ከስለላ ራስን መከላከል (SSD) በዓለም ዙሪያ ላሉ ሁሉ ራሳቸውን ከኤሌክትሮኒክ ስለላ እንዴት መከላከል እንደሚችሉ የሚያሳይ መመሪያ ነው። የእዚህ መመሪያ አንዳንድ ክፍሎች በጣም ትንሽ ቴክኒካል እውቀት ላላቸው ሰዎች ታቅደው የተሠሩ ሲኾኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ከፍተኛ የቴክኒክ ዕውቀት ያላቸውን ታዳሚዎች እና የግላዊነት/ደህንነት አሰልጣኞችን በማለም የተዘጋጁ ናቸው። የእያንዳንዱ ሰው የስጋት ሞዴል እንደሚኖርበት ከባቢ የተለያየ ነው። ማለትም ቻይና ከሚገኝ አራማጅ እስከ አውሮፓ ውስጥ እስከሚገኝ ጋዜጠኛ እንዲሁም ኡጋንዳ ውስጥ ካሉ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ማኅበረሰብ የተለያየ እንደኾነ እናምናለን። እያንዳንዱ ሰው ከመንግስት፣ ከቤተሰብ ወይም ሚስጥርን ለማወቅ ከሚሹ ቀጣሪዎች፣ ተከታታዮች፣ የውሂብ ቆፋሪ ኩባንያዎች፣ ወይም ከሚያጎሳቅለው የትዳር ጓደኛ የሚደብቀው የኾነ ነገር እንዳለ እናምናለን።

ይህ መመሪያ እንዲተገበር የሚመክረው ምንድን ነው? anchor link

በኢንተርኔት ላይ የሚገኙ እንደ ፓስወርድ ሴፍ ወይም VPN ወይም የቶር ብራውዘር በንድል ያሉ ስለ ተወሰኑ መሳሪያዎች አጠቃቀም የሚያስተምሩ ብዙ የግላዊነት እና የደህንነት መመሪያዎች አሉ። SSD የተለያዩ የግላዊነት እና የደህንነት መሣሪያዎችን አጫጫን እና አጠቃቀም ደረጃ በደረጃ የማስተማሪያ ቱቶሪያል የያዘ ነው። ከዚህም በተጨማሪም ስለ መስመር ላይ ግላዊነት እና ደህንነት እንዴት በተራቀቀ መንገድ ሰዎች ማስብ እንዳለባቸው፤ እንዲሁም በዙሪያቸው ያሉ መሳሪያዎች እና አጥቂዎች ቢቀያየሩ እንኳን ተገቢዎቹን መሣሪያዎች እና ልምዶች መምረጥን ለማስተማር እና አቅም ለመስጠት በማሰብ ታቅዶ የተዘጋጀ ነው። እባክዎን፤ ሕጉ እና ቴክኖሎጂው በፍጥነት ሊቀየር እንደሚችል እና የSSD የተወሰነ ክፍል ጊዜ ያለፈበት ሊኾን እንደሚችል ይገንዘቡ።

ይህ መመሪያ አንዳንድ በተለይ በጣም ጠንካራ እና የተወሳሰቡ ከኾኑ ስጋቶች ራስን መከላከል በጣም አዳጋች እና የማይቻል እንደኾነ ያገናዘባል። ማንኛውም ልዩ መሣሪያ ፍጹም ግላዊነትን እና ደህንነትን ይሰጣል የሚሉ ክርክሮችን በጥርጣሬ እንዲያዩ ተጠቃሚዎችን ግንዛቤ እንደሚያስጨብጥ ተስፋ እናደርጋለን። ጠንካራ የግላዊነት እና የደህንነት ልምምዶች ምንም እንኳን ከሁሉም ጥቃቶች መቶ ፐርሰንት ውጤታማነታቸውን ማረጋገጥ ባይቻልም ጠቃሚ ናቸው። እነዚህ ልምዶች የአጥቂውን ወጪ እና ድካም ያበዛሉ። በመኾኑም አጥቂዎ እርስዎን ከዚህ በላይ መሰለል ትርፉ ድካም እንደኾነ የሚያስብበት ደረጃ ላይ እስኪደርስ ወጪያቸው ሊጨምር ይችላል።

የመመሪያው ውስንነቶች ምንድን ናቸው? anchor link

ይህ መመሪያ ሰፋ ባለ አውድ የደህንነት አተገባበርን ወይም "OPSEC" አይመለከትም። OPSEC ማለት አንድ የጥቃት ዒላማ የኾነ ግለሰብ እንቅስቃሴዎች ለአጥቂው እንዳይደርስ የመከላከያ ሂደት ነው። ይህ አብዛኛውን ጊዜ ከዲጂታል ዓለም አልፎ የሚሄድ ሂደት ነው።

ለምሳሌ ምስጥራዊ የኾነ ስብሰባን ለማድረግ የሚጥሩ ሰዎች የኾነ ሰው በአካል ተከትሏቸው፣ ወይም በCCTV ካሜራዎች ታይተው፣ ወይም ጎረቤቶቻቸው ስለ ስብሰባቸው አውቀው፣ ወይም የመሰብሰቢያው ስፍራ በድምጽ መቅጃ ተጠምዶ እንደኾነ እና እንዳልኾነ ሊጨነቁ ይገባል። ምናልባት አጠራጣሪ እንቅስቃሴ ፈጥረው እንደኾነ ሊያስቡ ይገባቸዋል። በተጨማሪም አካላዊ የደህንነት ስጋት ሊኖሯቸው ይችላል። ቤታቸውን ሰብሮ የገባ ወይም ላፕቶፓቸውን የነካካ ግለሰብ መኖሩን መናገር ይችላሉ? ሚስጥራዊ ሰነዶቻቸው ደህንነትስ የተጠበቀ ነው?

እነዚህ የተወሰነ ዓይነት የደህንነት ፍላጎት ላላቸው ሰዎች በጣም አስፈላጊ እና ተገቢ የኾኑ ስጋቶች ቢኾኑም ነገር ግን በዚህ መመሪያ የማይካተቱ ቁምነገሮች ናቸው።

እባክዎን SSDን እጅግ ዘመናዊ ለኾኑ እውነታዎች፣ ኬዞች እና ዕውቀቶች ለሚያደርጉት ጥናት እንደ መነሻ ሰነድ ይጠቀሙት። እንዲሁም ስለ ሕግ የተጠቀሰው ነገር ትክክለኛ ቢኾንም በሌላ የሕግ ስርዓት (ቦታ) ትክክል ላይኾን እንደሚችል ይገንዘቡ። በተጨማሪም ሕጉ ተቀይሮ፣ ተሻሽሎ፣ ወይም በሌላ ተተክቶ ሊኾን እንደሚችል ይወቁ። በSSD የቀረቡ ቁም ነገሮች ዓላማቸው ለመረጃነት ብቻ እንጂ የሕግ የምክር አገልግሎት ለመስጠት አይደለም። በአካባቢዎ ፍቃድ ያለው ጠበቃን በማነጋገር ስለ እርስዎ ዓይነተኛ ጉዳይ ወይም ችግር ምክር ማግኘት ይኖርብዎታል።