የሚያጋጥምዎ አደጋዎችን መገምገም

የመስመር ላይ ደህንነትን ለመጠበቅ የሚያስችል ብቸኛ እና አንድ አማራጭ የለም። የዲጂታል ደህንነት የትኛውን መሣሪያ ይጠቀማሉ ከሚለው ይልቅ ሊያጋጥመኝ የሚችሉት ስጋቶች ምን እንደኾኑ መረዳት እና እነዚህ ስጋቶችን ለመከላከል ልወስዳቸው የምችላቸው እርምጃዎችስ ምንድን ናቸው የሚል መኾን ይኖርበታል። ደህንነትዎን በደንብ ለማረጋገጥ የትኛውን መረጃዎን መጠበቅ እንዳለብዎት እና ከማን ይህን መረጃ መከላከል እንዳለብዎት ማወቅ አስፈላጊ ነው። የዲጂታል ደህንነት ስጋቶች ከቦታ ቦታ፣ ከሥራ ባልደረባዎት እና ከሚሠሩት ሞያ ዓይነት አንጻር ሊለያይ ይችላል። በመኾኑም የመፍትሄ እርምጃዎች ከመውሰድዎ በፊት ለእርስዎ ተመጣጣኝ የኾነ ስጋትዎን የመገምገሚያ ሞዴል ያስፈልግዎታል።

የስጋትዎን ኹኔታ በሚገመግሙበት ወቅት በሚከተሉት አምስት ጥያቄዎች ራስዎን መመዘን ይኖርብዎታል፦ Anchor link

 1. ምንድን ነው መከላከል የምፈልገው?
 2. ከማን ነው መከላከል የምፈልገው?
 3. መከላከል ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
 4. ይሄንን መከላከል ባልችል ሊደርስብኝ የሚችለው አደጋ መጠኑ ምን ያህል ነው?
 5. ሊደርስብኝ ከሚችል አደጋ ራሴን ለመከላከል ምን ያህል ርቀት ለመሄድ ፈቃደኛ ነኝ?

ስለመጀመሪያው ጥያቄ በምንነጋገርበት ወቅት በአብዛኛው ጊዜ የምናስበው ስላካበትናቸው እሴቶች ወይም ከጥቃት ልንከላከላቸው ስለሚገቡን የዲጅታል ይዞታዎቻችን ነው። የዲጅታል ይዞታ ወይም እሴት የምንለው ዋጋ የምንሰጠውን እና ከአደጋ ልንከላከለው የምንፈልገውን ንብረታችንን ነው። ስለ ዲጂታል ደህንነት በምንነጋገርበት ወቅት እሴት ወይም ንብረት የምለው ነገር መረጃን እንደኾነ መታወቅ ይኖርበታል። ለምሳሌ የኢሜል ምልልስዎ፣ የአድራሻ ዝርዝርዎ፣ የፈጣን መልዕክት ልውውጥዎ እና የተለያዩ ሰነድዎ በሙሉ ንብረትዎት ናቸው። በተጨማሪም ኮምፒውተርዎ፣ ስልክዎ እና የመሳሰሉትም ንብረትዎት ናቸው።

የውሂቦትን/የዳታዎችትን ዝርዝር፣ የት እንደተቀመጠ፣ ማን መጠቀም እንደሚችል እና ሌሎች እንዳይጠቀሙት የሚከለክላቸው ምን እንደኾነ ይጻፉ።

ሁለተኛውን ጥያቄ ማለትም “ከማን ነው መከላከል የምፈልገው” የሚለውን ለመመለስ የእርስዎ እና የመረጃዎ አጥቂ ማን ሊኾን እንደሚችል ወይም የጥቃት ምንጭዎ ከየት እንደኾነ መረዳት አስፈላጊ ነው። የጥቃት ምንጭ በእሴት ወይም በእሴቶች ላይ ማንኛውንም ዓይነት ጥቃት ሊሰነዝር የሚችል ግለሰብ ወይም የተደራጀ አካል ነው። ለምሳሌ የመንግሥት አካል፣ መዝባሪዎች፣ ወይም የመስሪያ ቤት አለቃዎ አጥቂዎ ሊኾኑ ይችላሉ።

የእርስዎን ውሂብ ወይም የግንኙነት መረጃዎን ማግኘት የሚፈልግ ማን ሊኾን እንደሚችል ጥርጣሬ ውስጥ በማስገባት ዝርዝር ያውጡ። እነርሱም ግለሰቦች፣ የመንግስት አካላት ወይም ተቋማት ሊኾኑ ይችላሉ ።

ስጋት እንደ እሴት ወይም ንብረት በሚቆጥሩት መረጃዎ ላይ ሊከሰት የሚችል አደጋ ነው። አጥቂዎ በመረጃዎ ላይ ጉዳት ወይም አደጋ ሊያደርስ የሚችልባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ ግንኙነትዎ በኔትወርክ በሚተላለፍበት ወቅት አጥቂዎ የግንኙነትዎን ይዘት ሊያዳምጥ ወይም ሊያነብ፤ ወይም የግል ውሂብዎን ሊሰረዝ ወይም ሊያበላሽ ይችላል። በተጨማሪም የራስዎን ሰነድ ጥቅም ላይ ማዋል እንዳይችሉ ሊያደርግ ይችላል።

አጥቂዎች የሚያደርሱት ጥቃት የተለያየ እንደኾነ ሁሉ ጥቃት ለመሰንዘር የሚነሱበት አላማም እንዲሁ የተለያየ ነው። ለምሳሌ ፖሊስ ወይም የተለያዩ የሕግ አስፈጻሚ አካላት የፈጸሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያሳይ ቪዲዮ ቢኖርዎት መንግስት የእዚህን ቪዲዮ ስርጭት ለመቀነስ በማሰብ ቪዲዮውን ለማጥፋት ወይም ተደራሽነቱን ለመቀነስ ሊሞክር ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ፖለቲካዊ ባላንጣዎች እንዲህ ዓይነቱን ድብቅ መረጃ ያለ እርስዎ ዕውቀት በእጃቸው ማስገባት እና ማተም ይፈልጋሉ።

በመኾኑም አጥቂዎ በግል ውሂብዎ ማድረግ የሚፈልገው ምን ሊኾን እንደሚችል ይዘርዝሩ።

በተጨማሪም የአጥቂዎን ጥቃት የመሰንዘር አቅም እና ችሎታን ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት አስረላጊ ነው። ለምሳሌ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ያሉ የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት ሰጪዎች የስልክዎ መዝገብዎችን ሙሉ በሙሉ ማየት ስለሚችሉ ይህንን ውሂብ እርስዎን ለመጉዳት ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ክፍት የኾኑ የWi-Fi ኔትወርኮችን በሚጠቀሙበት ወቅት መዝባሪዎች ያልተመሰጠሩ ግንኙነትዎትን ሊያገኙ ይችላሉ። መንግታትም ይህን ማድረግ የሚያስችል የተሻለ አቅም ሊኖራቸው ይችላል።

በመጨረሻም ከግምት ውስጥ ሊያስገቡት የሚገባው ጉዳይ ሪስክ ወይም አደጋው የመከሰቱ አዝማሚያ ነው። አደጋው የመከሰቱ አዝማሚያ ወይም ሪስክ ማለት በአንድ እሴት ወይም ንብረት ላይ ሊደርሱ የሚችሉት ስጋቶች ምን ያህል የመፈጸም አዝማሚያ አላቸው ማለት ነው። ይህም ከአቅም ጋር ጎን ለጎን አብሮ የሚሄድ ነው። ምንም እንኳን የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት ሰጪዎች የእርስዎን ውሂብ ሙሉ በሙሉ የማግኘት አቅም ቢኖራቸውም የእርስዎን መልካም ስም ለማጉደፍ ኾን ብለው የግል ውሂብዎን በአደባባይ ላይ የመለጠፍ አዝማሚያቸው አናሳ ነው። ነገር ግን ይህ በኢትዮጵያ ኹኔታ ላይሰራ ይችላል።

በስጋት እና በአደጋው የመከሰቱ አዝማሚያ መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ ተገቢ ነው። ስጋት ሊከሰት የሚችለው ጉዳት ሲኾን አደጋው የመከሰቱ አዝማሚያ ወይም ሪስክ የሚባለው ደግሞ ይህ ስጋት ሊከሰት የሚችልበት አዝማሚያ ወይም የመኾን ዕድል ነው። ለምሳሌ መኖርያ ቤትዎ ሊደረመስ ይችላል የሚል ስጋት ሊኖርዎ ይህ ስጋት ግን በአፋር ሊከሰት የሚችልበት አዝማሚያ ወይም የመኾን ዕድል ከአዲስ አበባ በጣም ከፍ ያለ ነው።

አደጋው የመከሰቱ አዝማሚያ ወይም የመኾን ዕድል ትንተናን ማካሄድ ግለሰባዊ እና በግለሰቡ አመለካከት የተቃኘ ሂደት ነው። ሁሉም ሰው ተመሳሳይ ስጋትን የሚያይበት እና ቅድሚያ የሚሰጥበት መንገድ ተመሳሳይ አይደለም። በርካታ ሰዎች የተወሰኑ ስጋቶች የመከሰት አዝማሚያቸው ምንም ይሁን ምን ለመጋፈጥ ፈቃደኛ አይደሉም። ምክኒያቱም የስጋቱ መኖር ብቻ ከሚያስፈልጋቸው ዋጋ ጋር ሲወዳደር ሚዛን አይደፋም ብለው ስለሚያምኑ ነው። በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ግለሰቦች የአደጋው የመከሰት እድሉ ከፍተኛ ቢኾንም እንኳን ስጋቱን እንደ ችግር አያዩትም።

ለምሳሌ በወታደራዊ ስርዓት አውድ አንድ ንብረት ወይም እሴት በጠላት እጅ ከሚወድቅ እሴቱን መደምሰስ ወይም ማጥፋት የተሻለ አማራጭ ሊኾን ይችላል። ከዚህ በተቃራኒው በብዙ ሲቪላዊያን አውድ ደግሞ አንዳንድ እንደ ኢሜል ያሉ አገልግሎቶች ሚስጥራዊ ባይኾኑም እንኳ መኖራቸው በጣም አስፈላጊ ነው።

አሁን የስጋት ሞዴልን በተግባር እንለማመድ Anchor link

ቤትዎን እና በቤትዎ የሚገኘውን ንብረት ደህንነት ለማረጋገጥ ከፈለጉ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ማንሳት ይኖርብዎታል፦

 • በሬን መቆለፍ ይኖርብኛል?
 • ምን ዓይነት ቁልፎች መግዛት ወይም ማስገጠም ይኖርብኛል?
 • እጅግ ከፍ ያለ የደህንነት ስርዓት ያስፈልገኛል?
 • በዚህ አውድ ውስጥ ንብረቴ ምንድን ነው?
  • የቤቴ ግላዊነት
  • በቤቴ የሚገኙ ቁሳቁሶች
 • ስጋቱ ምንድን ነው?
  • ሰርጎ ገብ እንዳይገባ ነው
 • ሰርጎ ገብ ቤቴ የመገባቱ ትክክለኛ አዝማሚያ ምን ያህል ነው? ሊከሰት ይችላልን?

እነኚህን ጥያቄዎች እራስዎን ከጠየቁ በኋላ ምን ዓይነት እርምጃ መውሰድ እንዳለብዎት መመዘን ይችላሉ። ንብረትዎ እጅግ ውድ ከኾነ እና ሰርጎ ገቦች ቤትዎ የመግባት ዕድላቸው አነስተኛ ከኾነ ውድ ቁልፍ ለመግዛት ወጪ ማውጣት ተገቢ ነው ብለው ላያስቡ ይችላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ሰርጎ ገቦች ቤትዎ የመግባት እድላቸው ከፍ ያለ ከኾነ በገበያ ላይ አሉ የሚባሉትን ቁልፎች መግዛት እና ምን አልባትም አሉ የሚባሉ የደህንነት ስርዓቶችን መዘርጋት ይፈልጉ ይኾናል።

Last reviewed: 
2015-01-12
This page was translated from English. The English version may be more up-to-date.
JavaScript license information