Skip to main content
Surveillance
Self-Defense

ለእርስዎ ትክክለኛ የሆነውን ቪፒኤን መምረጥ

Last Reviewed: July 07, 2023

This page was translated from English. The English version may be more up-to-date.

ቪፒኤን ሲተነተን “ቨርቹዋል ፕራይቬት ኔትወርክ/ ምናባዊ የግል አውታረ መረብ ” ነው። ከአንድ ቪፒኤን ጋር ሲገናኙ፣ሁሉም እርስዎ የሚልኳቸው ውሂቦች (ለምሳሌ ድሩን ሲያስሱ ለመረጃ መቆጣጠርያዎቹ ሰርቨሮች የሚልኳቸውን ጥያቄዎች) ከእርስዎ የበይነመረብ አገልግሎት አቅራቢ ይልቅ ከቪፒኤኑ ከራሱ እንደሚነሱ ሆነው ነው የሚታዩት፡፡ ይህም የእርስዎን አይፒ አድራሻ ይደብቃል፡፡ የአይፒ አድራሻዎ የእርስዎን አጠቃላይ አድራሻ በመጠቆም እርስዎን ለመለየት ጥቅም ላይ ሊውል ስለሚችል የእርስዎን ግላዊነት በመጠበቅ ረገድ ጠቃሚ መሳሪያ ሊሆን ይችላል፡፡

ቪፒኤን በተግባር የሚከተሉትን ማድረግ ይችላል:

  • በተለይ በካፌ፣ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ቤተ መጻሕፍት ወይም በሌላ ቦታ ደህንነቱ ካልተጠበቀ የዋይ ፋይ አውታረ መረብ ሲገናኙ የበይነመረብዎን ተግባራት ማየት ከሚፈልጉ ዓይኖች ይጠብቃል። በዚህ ጊዜ አብዛኛው የበይነመረብ እንቅስቃሴ የሚመሰጠረው ኤችቲቲፒኤስን በመጠቀም ስለሆነ ይሄ የቪፒኤን አገልግሎት እምብዛም ወሳኝ አይሆንም፤ ነገር ግን በአንዳንድ ሁኔታዎች መሰረታዊ የበይነመረብ እንቅስቃሴዎን የኔትወርክ ኦፐሬተሩ ወይም የበይነመረብ አገልግሎት አቅራቢው እንዲያዩ ካልፈለጉ ቪፒኤን ጠቃሚ ይሆናል።
  • አንዳንድ ድረ-ገጾችን ወይም አገልግሎቶችን በሚዘጋ አውታረ መረብ ላይ የኢንተርኔት ሳንሱር ማድረግ። ለምሳሌ ከትምህርት ቤት የበይነመረብ ግንኙነት ወይም ይዘትን ከሚያግድ ሀገር ውስጥ ሲሰሩ። ማሳሰቢያ፡ የተወሰኑ ሀገሮችን የቪፒኤን ፖሊሲዎች አስመልክቶ ወቅቱን የጠበቀ የደህንነት መረጃ መያዝ ጠቃሚ ነው።
  • ከአገር ውጪ ሲጓዙ፣ በቤትዎ ፣ ወይም በማናቸውም ሰአት ከቢሮ ውጪ ሲሆኑ ከኮርፖሬት ኢንትራኔት ጋር ማገናኘት።

አንድ የተለመደ የተሳሳተ ግንዛቤ ቪፒኤኖች ለዴስክቶፕ ኮምፒውተሮች ብቻ ናቸው የሚለው ነው። ከስልክዎ ወደ እንግዳ ወይም ወደማያውቋቸው የዋይ-ፋይ ግንኙነቶች መግባት ልክ ከኮምፒውተርዎ ወደ እንግዳ የዋይ ፋይ አውታረመረብ እንደመግባት አደገኛ ሊሆን ይችላል። ከእርስዎ የበይነ መረብ አገልግሎት አቅራቢ የሚመጣውን እንቅስቃሴ2> ለማመስጠር በስልክዎ ላይ ቪፒኤን ሊኖርዎት ይችላል።

ከቪፒኤን ጋር በተያያዘ ለሁሉም የሚስማማ መፍትሄ የለም። ልክ እንደ ኢሜይል፣ ብዙ የቪፒኤን አገልግሎቶች ስላሉ ከነዛ ውስጥ ለእርስዎ የሚስማማውን አገልግሎት መምረጥ አለብዎት። በመረጡት ላይ በመመስረት እርስዎ በቀላሉ ከማያምኑዋቸው አውታረ መረቦች ጋር ሲገናኙ የተሻለ የደህንነት ደረጃ ካለው አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ። ይህ ማለት ግን እምነትዎን ቪፒኤን ላይ እየጣሉ ነው ማለት ነው።

ስለዚህ ቪፒኤን ይፈልጋሉ? እና የትኛውን ቪፒኤን መጠቀም አለብዎ? ይህ መመሪያ የትኞቹ መሳሪያዎች ለእርስዎ ትክክል እንደሆኑ እና ቪፒኤን ለማግኘት በሚፈልጉበት ጊዜ ግምት ውስጥ ማስገባት ያለብዎትን ነገሮች እንዲያስቡ ያግዝዎታል።

 በመሠረታዊ ነገሮች እንጀምር፡- ቪፒኤኖች እንዴት ይሰራሉ? anchor link

ቪፒኤን ሁሉንም የበይነ መረብ እንቅስቃሴዎን በመሳሪያዎችዎ እና በቪፒኤን መረጃ መቆጣጠርያ ሰርቨር መካከል ባለው "የተመሰጠረ ዋሻ" በኩል ያዞራል። ከዚያም እንቅስቃሴው ዋና የአይፒ አድራሻዎን በመደበቅ ከቪፒኤኑ ወደ መድረሻው ይሄዳል። ከድረገጹ አንጻር የእርስዎ መገኛ የቪፒኤን መረጃ መቆጣጠርያ ሰርቨሩ ባለበት ሁሉ ያለ ይመስላል። እንዲሁም ቪፒኤን የድር አሰሳዎን ከእርስዎ የበይነመረብ አገልግሎት አቅራቢ እና (እንደ ካፌ ወይም ሆቴል) ካለ የአካባቢው አውታረ መረብ ባለቤት ይደብቃል። ይህ አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም በበ2021 ሪፖርት መሰረት ኤፍቲሲ በአሜሪካ የሚገኙ የበይነመረብ አገልግሎት አቅራቢዎች እርስዎ ከሚጠብቁት በላይ የእርስዎን የአሰሳ መረጃ ለሶስተኛ ወገኖች እንደሚያጋሩ አግኝቷል። ሆኖም፣ አንድ ቪፒኤን የአሰሳ ውሂብዎን ከበይነመረብ አገልግሎት አቅራቢው ቢሰውርም፣ ለቪፒኤን አቅራቢው ሁሉም ይታያል።

ለተጨማሪ መረጃ፣ ከዲሞክራሲ እና ቴክኖሎጂ ማእከል የወጣው ይህ ጽሑፍ በይበልጥ ቴክኒካዊ ገጽታዎችን ይሸፍናል።

ሊታሰቡባቸው የሚገቡ ነገሮች፡ ቪፒኤኖች የማይሰሩት anchor link

ቪፒኤን የበይነመረብ እንቅስቃሴዎን በህዝብ አውታረመረብ ላይ ካለው ክትትል ይጠብቃል፤ ነገር ግን እርስዎ ከሚጠቀሙት የግል አውታረ መረብ ውሂብዎን አይከላከልም። የኮርፖሬት ቪፒኤን እየተጠቀሙ ከሆነ የኮርፖሬቱ አውታረ መረብ የሚመራው ማንኛውም ሰው እንቅስቃሴዎን ያያል። የንግድ ቪፒኤን እየተጠቀሙ ከሆነ አገልግሎቱን የሚመራ ማንኛውም ሰው እንቅስቃሴዎን ያያል።

የማይታመን የቪፒኤን አገልግሎት ሆን ብሎ የግል መረጃን ወይም ሌላ ጠቃሚ ውሂብ ለመሰብሰብ ይህን ሊያደርግ ይችላል።

የእርስዎ ኮርፖሬት ወይም የንግድ ቪፒኤን አስተዳዳሪ በአውታረ መረቡ ላይ የላኩትን መረጃ እንዲያስረክብ ከመንግሥታት ወይም ከህግ አስከባሪዎች ለሚመጣ ግፊት ተጋላጭ ሊሆን ይችላል። የቪፒኤን አገልግሎት አቅራቢዎ ውሂብዎን ለመንግሥታት ወይም ለህግ አስከባሪዎች ስለሚያስረክብበት ሁኔታ መረጃ ለማግኘት የቪፒኤን አገልግሎት አቅራቢዎን የግላዊነት ፖሊሲ መመልከት አለብዎት።

እንዲሁም የቪፒኤን አቅራቢው ስራ የሚሰራባቸውን ሀገሮችን ልብ ይበሉ።
 አቅራቢው የመንግስትን የመረጃ ማስተላለፍ ጥያቄዎችን የሚቆጣጠሩ ህጎችን ጨምሮ ለእነዚያ ሀገራት ህጎች ተገዢ ይሆናል።
 ህጎች ከሀገር ሀገር ይለያያሉ፤አንዳንድ ጊዜ እነዚያ ህጎች ሃላፊዎች እርስዎን ሳያሳውቁ ወይም ፈቃድዎን የመስጠት እድል ሳይሰጡዎት መረጃ እንዲሰበስቡ ያስችላቸዋል።
 የቪፒኤን አቅራቢው የሚሰራባቸው ሀገራት የህግ ድጋፍ ስምምነት ካላቸው ሀገራት ለሚመጡ የህግ ጥያቄዎች ተጋላጭ ሊሆን ይችላል።

አብዛኛዎቹ የንግድ ቪፒኤኖች ከእርስዎ ማንነት ጋር በቀላሉ ሊገናኝ በሚችል እና ለራስዎ ቪፒኤን አቅራቢ እንኳ ሊያሳዩ የማይፈሉጉትን መረጃ በሚይዝ ክሬዲት ካርድ ተጠቅመው ክፍያ እንዲከፍሉ ይጠይቃሉ። የክሬዲት ካርድ ቁጥርዎን ከንግድ ቪፒኤን አቅራቢዎ መጠበቅ ከፈለጉ የስጦታ ካርዶችን የሚቀበል የቪፒኤን አቅራቢን ይጠቀሙ :: ወይም ጊዜያዊ ወይም ተጠቅመው የሚጥሏቸው የክሬዲት ካርድ ቁጥሮችን ይጠቀሙ።
 እንዲሁም፣ አገልግሎቱን ሲጠቀሙ ምንም እንኳን አማራጭ የመክፈያ ዘዴ ቢጠቀሙም የቪፒኤን አቅራቢው አሁንም እርስዎን ለመለየት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችለውን አይ ፒ አድራሻዎን ሊሰበስብ እንደሚችል ልብ ይበሉ።
 የአይፒ አድራሻዎን ከቪፒኤን አቅራቢዎ መደበቅ ከፈለጉ፣ ከእርስዎ ቪፒኤን ጋር ሲገናኙ ቶርን መጠቀም ይችላሉ ወይም የብዙሃን አውታረ መረብን በመጠቀም ብቻ ከቪፒኤን ጋር ይገናኙ።

ቪፒኤን ማንነትን የሚደብቅ መሳሪያ አይደለም፡፡መገኛዎን እንዳያውቁ ከአንዳንድ ኩባንያዎች ሊከላከል ቢችልም፣ የሚከተሉትን በመጠቀም ኩባንያዎች እርስዎን ሊከታተሉ የሚችሉባቸው በዙ ሌሎች መንገዶች አሉ። እነዚህም ጂፒኤስን ጨምሮ የድር ኩኪዎች ፣ መከታተያ ፒክስሎች ፣ ወይም የጣት አሻራናቸው።

ለብዙ ሁኔታዎች ቪፒኤን ሊወሰድ የሚገባ በጣም አስፈላጊው የደህንነት እርምጃ አይደለም።
 በምትኩ፣ ጠንካራ የይለፍ ቃላትን በመጠቀም፣ ባለሁለት ደረጃ ማረጋገጫን ማቀናበርኤችቲቲፒኤስ ብቻእንዲሰራ ማድረግ፣ የሚጠቀሙትን መሳሪያ ማመስጠር የሶፍትዌር ማሻሻያዎችን ማድረግ እና መከታተያዎችን ማገድ፣ በበይነመረብ ላይ ራስዎን ለመጠበቅ የበለጡ ውጤታማ እርምጃዎች ናቸው።

ለእኔ ትክክል የሆነውን ቪፒኤን እንዴት ነው የምመርጠው? anchor link

ሁሉም ሰው ቪፒኤንን እንዴት ለመጠቀም እንደሚፈልግ የተለያየ ፍላጎት አለው። እናም የቪፒኤን አይነት እና ጥራት ከአንዱ አገልግሎት ወደ ሌላው በጣም ይለያያል። ለእርስዎ ትክክል የሆነውን ቪፒኤን ለማግኘት፣ በሚከተሉት መስፈርቶች መሰረት ቪፒኤንዎችን መገምገም ይችላሉ።

የይገባኛል ጥያቄዎች anchor link

የቪፒኤን አቅራቢዎቹ ስለምርታቸው ወይም አገልግሎታቸው የይገባኛል ጥያቄ እያቀረበ ነው? ምናልባት ምንም አይነት የተጠቃሚ ግንኙነት ውሂብ አላስገባም ብለው (ከዚህ በታች ያለውን የውሂብ ስብስብ ይመልከቱ) ወይም ውሂብ አናስተላልፍም ወይም አንሸጥም ብለው ይናገሩ ይሆናል። የይገባኛል ጥያቄ ዋስትና እንዳልሆነ ያስታውሱ፣ ስለዚህ እነዚህን የይገባኛል ጥያቄዎች ማረጋገጥዎን እርግጠኛ ይሁኑ።
 ምንም እንኳን ቪፒኤኑ በቀጥታ ለሶስተኛ ወገኖች ባይሸጥም እንኳን እንዴት ገቢ እንደሚፈጠር ዝርዝሮችን ለማግኘት የቪፒኤን አቅራቢውን የግላዊነት ፖሊሲ በጥልቀት ይመልከቱ። በቪፒኤን የግብይት ገጾች ላይ በግላዊነት ወይም ደህንነት ዙሪያ ያሉ ከፍተኛ ጥያቄዎችን ይከታተሉ፤ ምክንያቱም ማንኛውም የማይቻል የይገባኛል ጥያቄ የሚያቀርብ ቪፒኤን በሌሎች አካባቢዎች ታማኝ ላይሆን ይችላል።

እምነት እና ግልጽነት anchor link

የቪፒኤን አገልግሎት አቅራቢዎች አገልግሎታቸውን በተለይም በየዓመቱ ይፋ ከሚሆኑ ውጤቶች ጋር ለሶስተኛ ወገን ደህንነት ኦዲት ክፍት ማድረግ ይችላሉ ። ይህ ዓይነቱ ግልጽነት በቪፒኤን መተግበሪያዎች፣ የውሂብ መገኛ እና መሠረተ ልማት ውስጥ ያሉ የማይታወቁ የደህንነት ተጋላጭነቶችን ሊያሳይ ይችላል። እንደ አንድ ደንበኛ ሊሆን ለሚችል ተጠቃሚ፣ የቪፒኤን አቅራቢው ደህንነትን በቁም ነገር ለመመልከት እየሞከረ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ነው።
 ነገር ግን አሠራሮቹ ከኦዲት በኋላ ፣ በተለይም በመንግሥት ከተገደዱ፣ እንደማይለወጡ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም።

የቢዝነስ ሞዴል anchor link

ምንም እንኳን አንድ ቪፒኤን ውሂብዎን እየሸጠ ባይሆንም እንደምንም በስራ ላይ መቆየት መቻል አለበት። ቪፒኤኑ አገልግሎቱን የማይሸጥ ከሆነ፣ እንዴት አድርጎ ነው ስራውን ገበያ ላይ እንዲቆይ የሚያደርገው? እርዳታዎችን ይጠይቃል? የአገልግሎቱ የቢዝነስ ሞዴል ምንድን ነው? አንዳንድ ቪፒኤኖች በ"ፍሪሚየም" ሞዴል ይሰራሉ፤ ማለትም ለመቀላቀል ነፃ ናቸው ነገር ግን የተወሰነ የውሂብ ጣሪያ ከነኩ በኋላ ማስከፈል ይጀምራሉ። ቪፒኤኖች ሙሉ በሙሉ ነጻ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን የእርስዎን ውሂብ ይሸጣሉ። ተደጋጋሚ የደንበኝነት ምዝገባን ሊጠቀሙ ይችላሉ፤ ይህም መሰረዝን ከረሱ ማስከፈላቸውን ይቀጥላሉ።
 በጀትዎ ውስን ከሆነ፣ ይህ መታወቅ ያለበት ጠቃሚ መረጃ ነው።
 ከማስታወቂያ ማገድ የአሳሽ ቅጥያ በጣም ያነሰ ቁጥጥር ቢሰጡዎትም ቪፒኤኖች እንደ ማስታወቂያ እና መከታተያ እገዳ ያሉ ተጨማሪ ገጽታዎችን ሊያስቀምጡ ይችላሉ።

ዝና anchor link

ከቪፒኤኑ ጋር የተያያዙ ሰዎችን እና ድርጅቶችን መመርመር ጠቃሚ ነው። በደህንነት ባለሙያዎች የተረጋገጠ ነው? ቪፒኤኑ ስለራሱ የተፃፉ የዜና ዘገባዎች አሉት? ቪፒኤኑ በመረጃ ደህንነት ማኅበረሰብ ውስጥ በሚታወቁ ሰዎች የተቋቋመ ከሆነ እምነት የሚጣልበት የመሆን እድሉ ሰፊ ነው። ማንም ሰው የግል ማንነቱን ሊያስገባበት የማይፈልገውን አይነት አገልግሎት የሚያቀርብ ወይም ማንም በማያውቀው ኩባንያ የሚተዳደር የቪፒኤን አገልግሎት ከመጠቀም ይቆጠቡ። መስራቾቹን ወይም ሰራተኞቹን ይዘረዝር እንደሆነ ለማየት የቪፒኤኑን "ስለ እኛ" ገጽ መመልከት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። የአመራር ግልጽነት አንድ ኩባንያ ታዋቂ ለመሆኑ ዋስትና አይደለም፤ ነገር ግን ኩባንያው ታማኝነትን ለመመስረት እየሞከረ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ነው።

ውሂብ መሰብሰብ anchor link

በመጀመሪያ ውሂብን የማይሰበስብ አገልግሎት ያንን ውሂብ መሸጥ አይችልም።
 የግላዊነት ፖሊሲውን ሲመለከቱ፣ ቪፒኤኑ በእርግጥ የተጠቃሚ ውሂብን እንደሚሰበስብ እና እንደሚሸጥ ይመልከቱ።
 አንድ የቪፒኤን ኩባንያ በግላዊነት ፖሊሲው ውስጥ ካልከለከለው ውሂብዎን ሊመዘግብ ይችላል።
 እናም፣ እንደ ስልጣኑ፣ አንድ መንግስት ያንን ውሂብ ሊጠይቅ ወይም ለእሱ መጥሪያ ሊሰጥ ይችላል።

ምንም እንኳን አንድ ኩባንያ የግንኙነት ውሂብን አላስገባም ቢልም፣ ይህ ለጥሩ ባህሪ ዋስትና አይደለም.::
 ቪፒኤኑ በመገናኛ ብዙሃን የተጠቀሰባቸውን አጋጣሚዎች እንዲመረምሩ እናበረታታዎታለን። ደንበኞቻቸውን ሲያሳስቱ ወይም ሲዋሹ ተይዘው ሊሆን ይችላል።

ምስጠራ anchor link

የቪፒኤን ምስጠራ ምን ያህል ደህንነቱ የተጠበቀ ነው?
 አንድ ቪፒኤን እንደ ፖይንት ቱ ፖይንት ተነሊንግ ፕሮቶኮል (PPTP) አይነት የተሰበረ ምስጠራን እየተጠቀመ ከሆነ በእሱ ውስጥ የሚፈሰው ማንኛውም ውሂብ በእርስዎ የበይነመረብ አገልግሎት አቅራቢ ወይም ሀገር በቀላሉ ሊፈታ እና ሊታይ ይችላል።
 ቪፒኤኖቹ ከሁለት የተለያዩ ፕሮቶኮሎች ውስጥ አንዱን ማለትም ኦፐን ቪፒኤን እና ዋየርጋርድ መጠቀማቸውን ያረጋግጡ።

 ነገር ግን የኦፕን ቪፒኤን አጠቃቀም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየቀነሰ የመጣ ይመስላል፡፡ እናም አንዳንድ የቪፒኤን አቅራቢዎች የራሳቸውን የዋየርጋርድ አተገባበር ሊጠቀሙ ይችላሉ። የስራ ቪፒኤን እየተጠቀሙ ከሆነ፣ የእርስዎን የአይቲ ክፍል በማነጋገር ስለ ግንኙነቱ ደህንነት ይጠይቁ።

ኢኤፍኤፍ ለማናቸውም ቪፒኤን ወይም ደረጃዎች ሽፋን መስጠት አይችልም። አርአያነት ያለው የግላዊነት ፖሊሲ ያላቸው አንዳንድ ቪፒኤኖች መልካም ዓላማ በሌላቸው ሰዎች ሊመሩ ይችላሉ። የማያምኑትን ቪፒኤን አይጠቀሙ።

ያስታውሱ፡ ለሁሉም ይስማማል ተብሎ የሚወሰድ ቪፒኤን የለም። አንደን ቪፒኤንን ሲመርጡ ግምት ውስጥ ሊያስገቧቸው የሚገቡ ብዙ ምክንያቶች አሉ። ማንኛውንም ውሳኔ ከማድረግዎ በፊት የእርስዎን ዲጂታል ደህንነት ለመጠበቅ ስለሚጠቀሙባቸው መሳሪያዎች
 ሁልጊዜ የደህንነት እቅድዎን ግምት ውስጥ ማስገባትዎን ያስታውሱ።