Skip to main content
Surveillance
Self-Defense

ከተንቀሳቃሽ ስልኮች ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች

Last Reviewed: October 30, 2018

This page was translated from English. The English version may be more up-to-date.

የተንቀሳቃሽ ስልኮች በየቦታው የሚገኙ መሠረታዊ የመገናኛ መሳሪያዎች ኾነዋል። አሁን አሁን የተንቀሳቃሽ ስልኮች የድምጽ ልውውጥን ከማድረግ ባሻገር የኢንተርኔት አገልግሎትን ለመጠቀም፣ አጭር የጽሑፍ መልዕክትን ለመላክ፣ እንዲሁም የተለያዩ ኹነቶችን በማስታወሻነት ለመያዝ ይጠቅማሉ።

አለመታደል ኾኖ የተንቀሳቃሽ ስልኮች ዲዛይን የተደረጉበት መንገድ ደህንነት እና ግላዊነትን ታሳቢ በማድረግ አይደለም። ተንቀሳቃሽ ስልኮች የእርስ በእርስ ግንኙነትን አጋልጦ ከመስጠት ባሻገር ለተለያዩ ዘርፈ ብዙ ስለላዎች በተለይም ጆግራፊያዊ ቦታን ለመከታተል ያጋልጣሉ። ከዲስክቶፕ ወይም ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች ጋር ሲነጻጸሩ፤ ተጠቃሚዎች የተንቀሳቃሽ ስልኮችን የመቆጣጠር አቅማቸው እጅግ ውስን ነው። ስርዓተ ክወናቸውን መቀየር፣ የሸረኞች ሶፍትዌሮች ጥቃት ሲደርስ ጥናት አድርጎ እርምጃ መውሰድ፣ የማያስፈልጉ ሶፍትዌሮችን ማስወገድ፣ በተጨማሪም የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት ሰጪዎች በተጠቃሚው ላይ የሚያደርጉትን ስለላ መከላከል ከባድ ነው። ከዚህ ሁሉ ባሻገር ስልኮቹን የሚያመርተው ፋብሪካ ሶፍትዌሮቹን እና የደህንነት ዘዴዎችን ባለማዘመን የተንቀሳቃሽ ስልኮትን ከአግልግሎት ውጪ ሊያደርግ ይችላል። ይህ ከተከሰተ ሌላ የሚሄዱበት ቦታ የለም።

ከላይ ከተጠቀሱት ችግሮች መካከል ጥቂቶቹ የሶስተኛ ወገን የግላዊነት ሶፍትዌሮችን በመጠቀም ሊቃለሉ ይችላሉ። አንዳንዶቹ ግን ሊቃለሉ አይችሉም። ከዚህ ቀጥሎ የተንቀሳቃሽ ስልኮች እንዴት ስለላን እና ቁጥጥርን ሊተባበሩ/ሊያግዙ እንደሚችሉ እና የተጠቃሚዎችን ግላዊነት ሊጎዱ እንደሚችሉ እናሳያለን።

የአድራሻ ወይም የቦታ ክትትል anchor link

የተንቀሳቃሽ ስልኮች ከሚያደርሱት ከፍተኛ ጥልቀት ያለው እና የማይታየው የግላዊነት ስጋት ቀዳሚው ያሉበትን አድራሻ ሌት ተቀን በሚልኩት ሲግናል አማካኝነት ማሳወቃቸው ነው። የግለሰቦች የተንቀሳቃሽ ስልክ አድራሻ በሌሎች ሰዎች ክትትል ውስጥ ሊወድቅ የሚችልባቸው ቢያንስ አራት መንገዶች አሉ።

1. የተንቀሳቃሽ ስልክ የሲግናል ክትትል— ምሶሶዎች anchor link

በሁሉም ዘመናዊ የተንቀሳቃሽ ስልክ አውታረ መረቦች የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት ሰጪው በአውታረ መረቡ ውስጥ እያንዳንዱ የተንቀሳቃሽ ስልክ የት ሃይል እንዳለው እና እንደተመዘገበ በማስላት የስልኩን ስፍራ ወይም አድራሻ ማወቅ ይችላል። ይህን ማድረግ የተቻለው የተንቀሳቃሽ ስልክ መስመሮች የተዘረጉበት መንገድን መሰረት በማድረግ ነው። ይህ በእንግሊዝኛው ትራያንጉሌሽን ይባላል።

ይህንን የተንቀሳቃሽ ስልክ ሥፍራ ማወቂያ አንደኛው መንገድ አገልግሎት ሰጪው የአንድ ደምበኛን የተንቀሳቃሽ ስልክ ከተለያዩ ምሶሶዎች አንጻር ያለውን የሲግናል ጥንካሬ በማስተዋል እና ይህንን አይነት ውጤት ለመስጠት ስልኩ የት ሥፍራ ሊኾን እንደሚችል በማስላት ነው። አገልግሎት ሰጪው የአንድን ደምበኛ ስፍራ በትክክል የማወቁ ጉዳይ በተለያዩ ምክኒያቶች ሊለያይ ይችላል። ከነዚህም መሃል የአገልግሎት ሰጪው የሚጠቀመው ቴክኖሎጂ እና በአንድ አካባቢ ያለው የምሶሶዎች ብዛት ይገኙበታል። አብዛኛውን ጊዜ በሰፈር ደረጃ የማወቅ ትክክለኝነት ሲኖረው በአንዳንድ ስርዓት ከሰፈር በዘለለ በአቅራቢያ ትክክለኝነትን የማወቅ አቅም ሊኖረው ይችላል።

የተንቀሳቃሽ ስልክዎ በአገልግሎት ላይ እስካለ እና ሲግናልን ለአግልግሎት ስጪው አውታረ መረብ እያስተላለፈ እስከኾነ ድረስ ከዚህ ዓይነቱ ክትትል የማምለጫ ወይም የመደበቂያ መንገድ የለም። ምንም እንኳ ይሄንን ማድረግ የሚችለው የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያው ብቻ ቢሆንም መንግስት የተጠቃሚዎችን አድራሻ ውሂብን (የአሁን ጊዜ ይኹን ያለፈ ጊዜ) አገልግሎት ሰጪውን በማስገደድ ሊረከብ ይችላል። በኢትዮጵያ ሁኔታ የስልክ አገልግሎት የሚሰጠው የመንግስት ኩባንያ ስለሆነ መንግስት ኩባንያውን ማስገደድ አይጠበቅበትም። በ2003 ጀርመናዊው የግላዊነት አራማጅ ማልት ስፒትስ የጀርመንን የግላዊነት ሕግ በመጠቀም የስልክ አገልግሎት የሚሰጠው ኩባንያው ዘንድ ያሉትን መዝገቦች ሁሉ እንዲያስረክቡት አስገድዷቸዋል። ይህንም የተንቀሳቃሽ ስልክ አግልግሎት ሰጪዎች ተጠቃሚዎችን እንዴት እንደሚከታተሉ ለሌሎች ሰዎች ለማሳየት በትምህርታዊ ሪሶርስነት አትሞታል። (ይህንን በመጎብኘት የአገልግሎት ሰጪው ስለ እሱ ምን እንደሚያውቁ ማየት ይችላሉ።) መንግስት ይህን ዓይነቱን ውሂብ ያገኛል ማለት ሐልዮታዊ ሳይሆን እንደ አሜሪካ ባሉ አገራት በብዛት በህግ አስፈጻሚ አካላት ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኝ ስርዓት ነው።

ሌላኛው ተያያዥነት ያለው እና መንግስት ከተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት ሰጪዎች የተጠቃሚዎችን መረጃ ለማገኘት የሚጠቀምበት መንገድ በእንግሊዝኛው አጠራር "ታወር ደምፕ" ይባላል። በዚህ ጊዜ መንግስት በአንድ አካባቢ እና ጊዜ የተገኙ ሁሉንም የተንቀሳቃሽ ስልኮች ዝርዝር እንዲሰጠው የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት ሰጪውን ይጠይቃል። ይህ ወንጀልን ለመርመር ወይም በተቃውሞ ሰልፍ ላይ ማን እንደተሳተፈ ለማወቅ ሊጠቅም ይችላል። (በተደጋጋሚ የዩክሬን መንግስት ይህንን ታወር ደምፕ የተባለውን ዘዴ በ2007 ለዚህ ጥቅም በማዋል መንግስትን በመቃወም በተደረገው ትዕይንተ-ሕዝብ ላይ የተንቀሳቃሽ ስልካቸውን በመቆጣጠር በሥፍራው የተገኙ ሰዎችን ስም ዝርዝር ለማወቅ ተጠቅሞበታል።)

በተጨማሪ የተጠቃሚዎች ስልክ የት አካባቢ እየተገናኘ እንዳለ ለማወቅ አንደኛው አገልግሎት ሰጪ ከሌላው ጋር የተጠቃሚዎችን ውሂብ ይለዋወጣል። ምንም እንኳን ይህ ውሂብ ከተለያዩ የሞባይል ምስሶውች ውሂብን በመሰብሰብ እንደሚደረገው ክትትል ትክክለኛ ባይሆንም እያንዳንዱ የተንቀሳቃሽ ስልክ ቀፎን ለመከታተል ለሚደረግ መሰረታዊ አገልግሎት ሊውል ይችላል። ይህም የተንቀሳቃሽ ስልክ መስመሩ የት ሥፍራ ሆኖ ከተንቀሳቃሽ ስልክ አውታረ መረቡ ጋር እንደተገናኘ መረጃን በመሰብሰብ እና ለመንግስት ወይም ለግል ተጠቃሚዎች ውጤቱን የመስጠትን የንግድ አገልግሎት ይጨምራል። (ዘ ዋሽንግተን ፖስት የተሰኘው ጋዜጣ ይህ የክትትል መረጃ እንዴት በቀላሉ ሊገኝ እንደሚችል ዘግቧል።) እንደ ቀደመው የመከታተያ መንገድ ይህ የመከታተያ ብልሃት የተንቀሳቃሽ ስልክ አግልግሎት ሰጪዎች የተጠቃሚዎች ውሂብን እንዲሰጡ አያስገድድም። ይልቁንም ይህ ዘዴ በንግድ አማካኝነት የሚገኘውን የሥፍራ ውሂብን ይጠቀማል።

2. የተንቀሳቃሽ ስልክ ክትትል — IMSI ካቸር anchor link

መንግስት ወይም ሌላ በከፍተኛ የቴክኒክ ደረጃ ላይ ያለ ድርጅት፤ እንደ IMSI ካቸር ያሉ መሳሪያዎችን በመጠቀም፤ የስፍራ ውሂብን በቀጥታ መሰብሰብ ይችላል። (IMSI ካቸር ወይም ጠላፊ እውነተኛ ምስሶ መስሎ የሚሰራ በቀላሉ የሚጓጓዝ የሀሰት የተንቀሳቃሽ ስልክ ምሰሶ ሲሆን የአንድ ሰው የተንቀሳቃሽ ስልክ መስመርን ለ“መጥለፍ” እና በአካባቢው መገኘቱን ለመመርመር እና/ወይም ግንኙነቱን ለመሰለል አግልግሎት ይውላል።) IMSI የሚለው ኢንተርናሽናል የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች እንደማለት ነው። ይህ ማለት የእያንዳንዱን ተጠቃሚ የሲም ካርድ ማንነትን ያሳያል። በተጨማሪም IMSI ካቸር የመሳሪያዎችን ሌሎች ባሕሪያት በመጠቀም መሳሪያዎቹን ኢላማ ውስጥ ሊያስገባ ይችላል።

በአንድ ሥፍራ ያሉ መሳሪያዎችን ለመቆጣጠር የIMSI ካቸርሩ ወይም ጠላፊው ወደዚያ ሥፍራ ወይም አካባቢ መወሰድ አለበት። በአሁኑ ሰዓት አስተማማኝ የሆነ ከIMSI ካቸር መከላከያ ዘዴ የለም። (አንዳንዶች መተግበሪያዎች በሥፍራው የIMSI ካቸር ወይም ጠላፊ እንዳለ እንደሚያሳዩ ቢጠቁሙም ነገር ግን ጥቆማው ትክክለኛ አይደለም።) በሚፈቅዱ መሳሪያዎች ላይ የ2ጂ ድጋፍን ማቦዘን (ይህም መሳሪያው ከ3ጂ እና ከ4ጂ አውታረ መረብ ጋር ብቻ እንዲገናኝ ያደርጋል) እና ከአገለግሎት ሰጪዎ የአግልግሎት ከባቢ ውጪ የማይወጡ ከሆነ የሮሚንግ አገልግሎትን ማቦዘን ጥቅም ሊኖረው ይችላል። ይህ እርምጃ ከአንዳንድ ዓይነት የIMSI ካቸሮች ጥቃት ሊከላከል ይችላል።

3. የWi-Fi እና የብሉቱዝ ክትትል anchor link

ዘመናዊ ስማርት ስልኮች ከተንቀሳቃሽ ስልክ አውታረ መረብ ገጽታ በተጨማሪ ሌሎች የራዲዮ አስተላላፊዎች አሏቸው። አብዛኞቹ የWi-Fi እና የብሉቱዝ ማስተላለፊያ አቅም አላቸው። እነዚህ ሲግናሎች የሚተላለፉት ከተንቀሳቃሽ ስልክ ሲግናል ባነሰ ሃይል ሲሆን የሲግናሉም ተቀባይነት በአጭር ርቀት (ለምሳሌ በአንድ ክፍል ውስጥ ወይም በአንድ ህንጻ ወስጥ ከሆኑ) ውስጥ ብቻ ነው። አንዳንድ ጊዜ ወሰብሰብ ያለ አንቴናን በመጠቀም ካልተጠበቀ ሩቅ ስፍራ እነዚህን ሲግናሎች ማግኘት ይቻላል። በ2000 የቬንዙዌላ ተመራማሪ ትንሽ የራዲዮ ጣልቃ ገብነት ባለው ገጠራማ ሁኔታ ውስጥ እጅግ ሩቅ ከሆነ 382ኪሜ ወይም 237ማይል ርቀት የWi-Fi ሲግናልን ማግኘት እንደሚቻል አሳይቷል። እነኚህ ሁለት ገመድ አልባ የሲግናል አይነቶች በመሳሪያው ላይ ለየት ያለ መለያ ቁጥር ያላቸው ሲሆን ይህም ቁጥር የMAC አድራሻ ይባላል። ይህ የMAC አድራሻ ሲግናሉን በሚቀበል በማንኛውም ሰው ሊታይ ይችላል። ይህ አድራሻ የተሰጠው የመሳሪያው አምራች መሳሪያውን በሰሩበት ወቅት ሲሆን ከስማርት ስልኮች ጋር የሚመጡ ስፍትዌሮችን በመጠቀም መቀየር አይቻልም።

እንዳለመታደል ሆኖ ስልኩ ከገመድ አልባ አውታረ መረብ ጋር ባይገናኝም ወይም ውሂብን እያስተላለፈ ባይሆንም እንኳን የMAC አድራሻው በገመድ አልባ ሲግናሎች ሊታይ ይችላል። በአንድ ስማርት ስልክ ላይ Wi-Fi በሚበራበት ወቅት ስማርት ስልኩ የMAC አድራሻውን የያዘ ሲግናሎችን ያስተላልፋል። ስለዚህም በዙሪያው ያሉ ሰዎች የMAC አድራሻውን በማየት ስልኩ በአካባቢው እንዳለ ይረዳሉ። ይህም ለንግድ ክትትል መተግበሪያዎች ጥቅም ላይ ውሏል። ለምሳሌ የመደብር ሻጮች ይህንን በመጠቀም አንድ ደምበኛ ስንት ጊዜ መደብራቸውን እንደጎበኘ እና ምን ያህል ሰዓት በመደብራቸው እንደቆየ መረጃ ይሰበስቡበታል። ከ2006 ጀምሮ የስማርት ስልክ አምራቾች እንደዚህ አይነቶቹ ክትትሎች ችግር እንደሚያመጡ ተገንዝበዋል። ነገር ግን ይህ ችግር የሚፈታበት ጊዜ ቅርብ አይደለም፤ መፈታት ከተቻለ።

ከGSM ክትትል ጋር ሲነጻጸር እንደዚህ ዓይነት ክትትሎች ለመንግስት ስለላ እምብዛም ጥቅም የላቸውም። ይህም የሆነበት ምክንያት በደንብ የሚሰሩት በአጭር እርቀት ውስጥ ስለሆነ እና በቅድሚያ መከታተል የሚፈልጉት ሰው የሚጠቀመው ስልክ የMAC አድራሻን ማወቅ ስለሚያስፈልግ ነው። ነገር ግን ይህ ዓይነቱ ክትትል እጅግ ከፍ ያለ ትክክለኝነት ሊኖረው ይችላል። ለምሳሌ አንድ ሰው ህንጻ ውስጥ ሲገባና እና ሲወጣ ማወቅ ይችላሉ። ምንም እንኳን እነዚህን ቴክኖሎጂዎች አብዝተው መጠቀም ለሚፈልጉ ሰዎች አመቺ ባይሆንም በስማርት ስልኩ ላይ የWi-Fi እና ብሉቱዝ አገልግሎቱን ማጥፋት ከዚህ አይነቱ ክትትል ሊከላከል ይችላል።

የWi-Fi አውታረ መረብ ሰራተኞች አውታረ መረቡን የተቀላቀለ የእያንዳንዱን ስልክ የMAC አድራሻ ማየት ይችላሉ። ይህ ማለት በጊዜ ሂደት አንድ ስልክን መለየት እንደሚችሉ እና አውታረ መረቡን ከዚህ በፊት ተገናኝተው የሚያውቁ ተመሳሳይ ሰው መሆንዎን እና አለመሆንዎን ሊያውቁ ይችላሉ (ምንም እንኳን ስምዎትን ወይም የኢሜል አድራሻዎን የትም ባያስገቡ ወይም ወደ ማንኛውም አግልግሎት ባይገቡ)።

በጥቂት ስልኮች ላይ የMAC አድራሻን መቀየር ይቻላል። ይህም ሌሎች ሰዎች የWi-Fi መሳሪያዎትን ከጊዜ ብዛት በቀላሉ መለየት እንዳይችሉ ያደርጋል። በእነዚህ መሳሪያዎች ላይ ትክክለኛ ሶፍትዌር እና አወቃቀር በመምረጥ እዲስ እና የተለየ የMAC አድራሻን በየቀኑ መምረጥ ይቻላል። በስማርት ስልኮች ላይ ይህን ለማድረግ በተለምዶ ለየት ያለ ሶፍትዌር ያስፈልጋል። እነኚህ ሶፍትዌሮችም የMAC አድራሻ ቀያሪ መተግበሪያ በመባል ይታወቃሉ። በአሁኑ ሰዓት ለአብዛኛው የስማርት ስልክ ሞዴሎች ይህ አማራጭ የለም።

4. ከድር ማሰሻ እና ከመተግበሪያዎች የሚሾልክ የመገኛ ሥፍራ መረጃ anchor link

አብዛኞቹ ዘመናዊ የስማርት ስልኮች ስልኩ ያለበትን ስፍራ ማወቅ እንዲችል መንገዶችን ይሰጣሉ። አብዛኛውን ጊዜ GPSን በመጠቀም ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሌሎች የGPS ኩባንያዎች የሚሰጧቸውን አግልግሎቶች በመጠቀም ነው። እነኚህ የGPS ኩባንያዎች ስልኩ ካለበት ቦታ የሚያያቸውን የተንቀሳቃሽ ስልክ ምሶሶዎችን እና/ወይም የWi-Fi አውታረ መረብ ዝርዝሮችን መሰረት በማድረግ ኩባንያው የስልኩ ስፍራ የት እንደሆነ እንዲገምት የሚጠይቁ ናቸው። እንደ ማፕ ያሉ ያሉበትን ስፍራ በካርታ ላይ የሚያሳዩ መተግበሪያዎች ይህንን የስፍራ መረጃ ስልኩን በመጠየቅ ስፍራውን ያማከለ አግልግሎት ለመስጠት ይጠቀሙበታል።

ከእነኚህ መተግበሪያዎች አንዳንዶቹ ያሉበትን ሥፍራ በአውታረ መረቡ አማካኝነት ለአግልግሎት ሰጪው ያስተላልፋሉ። ይህም ለሌሎች ሰዎች እርስዎ ላይ ክትትል የማድረጊያ መንገድን ይከፍትላቸዋል። (የዚህ መተግበሪያ ሠሪዎች ይህንን መተግበሪያ የሠሩት ተጠቃሚዎች ላይ ክትትል የማድረግ ፍላጎት ኖሯቸው ላይሆን ይችላል። ይሁንና ይህንን ዓይነት ችሎታ ያለው ሶፍትዌር ሰርተው ሲያበቁ እና የተጠቃሚዎቻቸውን የሥፍራ መረጃ ለመንግስት እና ለመዝባሪዎች ሊሰጡ ይችላሉ።) አንዳንድ ስማርት ስልኮች ስልክዎት ያለበትን ስፍራ መተግበሪዎች ማወቅ እንዳለባቸው ወይም እንደሌለባቸው መቆጣጠር የሚያስችል አቅም ይሰጥዎታል። የትኛው መተግበሪያ ይህንን መረጃ ማየት እንደሚችል ለመገደብ መሞከር፣ እና በትንሹ የቦታ መረጃዎን የሚያጋሩት ከሚያምኗቸው እና ያሉበትን ቦታ ለማወቅ በቂ ምክኒያት ካላቸው መተግበሪያዎች ጋር ብቻ መሆኑን ማረጋገጥ ጥሩ የግላዊነት ልምምድ ነው።

በአንዳንድ ኹኔታዎች ልክ አስደሳች ፊልም ላይ እንደሚሆነው አንድን ሰው የሚከታተሉ ሰዎች ሰውየውን መንገድ ለመንገድ ሲከታተሉ እንደሚታየው የስፍራ መከታተያ ዓላማ አንድ ግለሰብ በአሁኑ ወቅት የት እንዳለ ለማወቅ ብቻ አይደለም። ከዚያም አልፎ ስለ ሰዎቹ ታሪካዊ እንቅስቃሴያቸው እና ዕምነታቸው፣ በየትኞቹ ሁነቶች እንደተሳተፉ፣ እና የግል ግንኙነቶቻቸው ላይ ያለ ጥያቄን ለመመለስ ሊሆን ይቻላል። ለምሳሌ የሥፍራ ክትትል ሰዎች የፍቅር ግንኙነት እንዳላቸው እና እንደሌላቸው ለማወቅ፣ እነማን አንድ ልዩ ስብሰባ እንደተሳተፉ ለማወቅ ወይም ደግሞ በአንድ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ማን እንደተሳተፈ፣ ወይም የአንድ ጋዜጠኛ ሚስጥራዊ ቃል አቀባይ ማን እንደሆነ ለማወቅ ጥቅም ሊውል ይቻላል።

ዋሽንግተን ፖስት የተሰኘው ጋዜጣ በታህሳስ 2006 ብዙ መረጃን መሰብሰብ በሚያስችሉት የNSA በሥፍራ ክትትል መሳሪያዎች አማካኝነት የስልክ ኩባንያዎችን መሰረተ ልማት አውታሮች በመጠቀም/በመጥለፍ የትኛው ስልክ ከየትኛው የስልክ ምሰሶ ጋር መቼ እንደሚገናኝ “በአለም አቀፍ ያሉ የተንቀሳቃሽ ስልኮች የት እንዳሉ የሚያሳይ” ዘገባ አቅርቧል። ኮ-ትራቭለር የተባለው መሳሪያ ይህንን ውሂብ ተጠቅሞ በተለያዩ ሰዎች እንቅስቃሴ መካከል ያለውን ግንኝነት ለማወቅ (የየትኞቹ ሰዎች መሳሪያዎች አብረው እንደሚንቀሳቀሱ እና በተጨማሪም አንድ ሰው ሌላን ሰው መከታተሉን እና አለመከታተሉን ለማወቅ) ያስችላል።

ስልክን ማጥፋት anchor link

ስልኮች የስልክ ጥሪ አገልግሎት ጥቅም ላይ ባይውሉ እንኳን ሰዎችን ለመከታተል ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ በሰፊው ይወራል። በዚህም የተነሳ ሰዎች ስሱ የሆኑ መረጃዎችን በሚወያያዩበት ሰዓት ሰልኮቻቸውን ሙሉ በሙሉ ዘግተው ወይም በስልኮቻቸው ውስጥ ያሉትን ባትሪዎች አውጥተው መሆን እንዳለበት ይነገራል።

ባትሪውን እንዲያወጡ የሚመከርበት ዋነኛው ምክንያት ስልኩ ባዘዙት መሰረት የተዘጋ አስመስለው የሚያሳዩ (ጥቁር እስክሪን በማሳየት) ነገር ግን ስልኩ ሳይዘጋ ክፍት ሆኖ ውይይትን መቆጣጠር ወይም ሳይታይ ስልክ መደወልን ወይም መቀበልን እንዲችል የሚያደርጉ ሸረኛ ሶፍትዌሮች በመኖራቸው ነው። በመሆኑም ተጠቃሚዎች ስልካቸው በትክክል ሳይጠፋ የጠፋ እንደሆነ በማሰብ ሊታለሉ ይችላሉ። ምንም እንኳን ምን ያህል በተሳካ ሁኔታ እንደሚሰራ እና ምን ያህል ጥቅም ላይ እንደዋለ በርካታ መረጃ ባይኖረንም ይህ አይነቱ ሸረኛ ሶፍትዌር ቢያንስ በተወሰኑ መሳሪያዎች ላይ ይሰራል።

ስልክን ማጥፍት የራሱ የጎንዮሽ ጉዳት አለው። ይህም በተመሳሳይ ሰዓት በአንድ ሥፍራ ያሉ የብዙ ሰዎች ስልክ በአንድ ላይ ሲጠፋ ለተንቀሳቃሽ ስልክ አግልግሎት ሰጪው ስልካቸውን ሊያስጠፋ የተገባው የሆነ ነገር እንዳለ ጥርጣሬን ሊያጭር ይችላል። (ይህም ነገር ምናልባት በቲያትር ቤት ውስጥ ፊልሙ ጀምሮ ሊሆን ይችላል፣ ወይም ኤርፖርት ውስጥ የአውሮፕላን መነሳትን ተከትሎ ሊሆን ይችላል፣ ወይም ደግሞ ስሱ የሆነ ስብሰባ ወይም ውይይት እያካሄዱ ሊሆን ይችላል።) ትንሽ መረጃን የሚሰጥ ሌላው አማራጭ መንገድ ደግሞ የሁሉንም ሰው ስልክ የስልኮቹ ማይክሮፎን ድምጽ መመዝግብ በማይችልበት ስፍራ ወይም ክፍል ውስጥ መተው ነው።

ጊዜያዊ ወይም በርነር ስልኮች anchor link

ለጊዜው ጥቅም ላይ የሚውሉ እና ከዚያም በኋላ የሚጣሉ ስልኮች አብዛኛውን ጊዜ በርነር ፎንስ ወይም ጊዜያዊ ስልኮች በመባል ይጠራሉ። ብዙ ጊዜ የመንግስት ስለላን ለመከላከል የሚሞክሩ ሰዎች ስልካቸውን (እና የስልክ መስመር ቁጥራቸውን) በብዛት በመቀያየር ግንኙነታቸውን ማወቅ አዳጋች ለማድረግ ይሞክራሉ። የቅድመ ክፍያ ስልኮች (ከግላዊ የባንክ አካውንታቸው ጋር ግንኙነት የሌለው) በመጠቀም የተንቀሳቃሽ ቀፎዎቹም ሆኑ ሲም ካርዶቹ ከማንነታቸው ጋር ያልተመዘገቡ/ያልተገናኙ መሆኑን ያረጋግጣሉ። በአንዳንድ አገራት ይህ በግልጽ የተቀመጠ ሲሆን በሌሎች አገራት ግን ማንነትን ሳያሳውቁ የተንቀሳቃሽ ስልክ አግልግሎት ማግኘት ሕጋዊ ወይም የአፈጻጸም ችግር ሊኖረው ይችላል።

ይህ ቴክኒክ የተወሰኑ ውስንነቶች አሉበት

አንደኛ የተንቀሳቃሽ ስልክ አውታረ መረቡ ሲም ካርዱን እና ቀፎውን በአንድነት ስለሚመለከት ሲም ካርዶችን በዘፈቀደ መቀያየር ወይም ሲም ካርድን ከአንድ መሳሪያ ወደሌላ መሳሪያ መቀያየር የሚሰጠው ጥበቃ በጣም አነስተኛ ነው። በሌላ አገላለጽ የአውታረ መረብ አገልግሎት ሰጪው የትኛው ሲም ካርድ በየትኛው መሳሪያ ወይም ቀፎ ውስጥ ጥቅም ላይ እንደዋለ ታሪኩን ስለሚያውቅ እና ሲም ካርዱን እና ቀፎውን ለየብቻ ወይም ሁለቱንም በአንድ ላይ መከታተል ስለሚችል ነው። ሁለተኛ መንግሥታት የሥፍራ ክትትልን ተጠቅመው ፍንጭ ወይም መላምት ሊሰጣቸው የሚችል የተንቀሳቃሽ ስልክ ስፍራ ማወቂያ ተንታኝ ቴክኒክን ሲሰሩ ቆይተዋል። ይህ ዘዴም ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ መሳሪያዎች የአንድ ሰው መሆናቸውን ወም አለመሆናቸውን ማወቅ የሚያስችላቸው ነው።

ይህንን ማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ዘዴዎች አሉ። ለምሳሌ አንድ ተንታኝ ሁለት መሳሪያዎች በአንድ ላይ እንደሚሄዱ እና እንደማይሄዱ ወይም ሁለቱም በተመሳሳይ ጆግራፊያዊ ቦታ ላይ መገኘታቸውን ማጣራት (ምንም እንኳን ሁለቱም በተለያየ ጊዜ ጥቅም ላይ ቢውሉም) ይችላል።

ሌላው በተሳካ ሁኔታ ማንነትን ሳያሳውቁ የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎትን መጠቀምን አዳጋች የሚያደርገው የእያንዳንዱ ሰው የአደዋወል ዘይቤ በጣም የተለያየ መሆኑ ነው። ለምሳሌ በልምድ በብዛት ለቤተሰብ አባላት እና ለስራ ባልደረቦችዎ ሊደውሉ ይችሉ ይሆናል። እነኚህ ሰዎች የስልክ ጥሪ የሚቀበሉት ከተለያየ ወገን ሊሆን ቢችልም በብዛት ከተመሳሳይ የስልክ ቁጥር ለሁለቱም ስልክን የሚደውሉት ወይም የስልክ ጥሪ የሚያደርጉት ብቸኛው ሰው እርሶ እንደሆኑ ማወቅ ይቻላል። ስለሆነም ባጋጣሚ ስልክ ቁጥርዋን ቢቀይሩም እንኳን ተመሳሳይ የስልክ ጥሪ እና አቀባባል ዘይቤን የሚከተሉ ከሆነ እርስዎ የሚጠቀሙት አዲስ ስልክ ቁጥር የቱ እንደሆነ በጣም በቀላሉ ማወቅ ይቻላል። ያስተውሉ እዚህ ድምዳሜ ላይ የሚደረሰው እርስዎ የደወሉትን አንድ የስልክ ቁጥርን መሰረት በማድረግ ብቻ ሳይሆን የደወሏቸውን የተለያዩ ለየት ያሉ የስልክ ቁጥር ቅንብሮችን በማየት ነው። (በርግጥ የስልክ ምዘገባን በመጠቀም “በተመሳሳይ ሁኔታ ለተወሰኑ ሰዎች” የስልክ ጥሪን ከአዲስ የስልክ ቁጥሮች ያደረጉ ሰዎችን ለማወቅ ፕሮቶን የተሰኘው የአሜሪካን መንግስት ስርዓት ይህንን ማድረጉን ዘ ኢንተርሴፕት ዘግቧል።) ተጨማሪ ምሳሌ በሄሜስፊር የአሜሪካ መረጃ የማግኘት መብትን (FOIA) ተጠቅሞ ያገኘውን ሰነድ ማየት ይቻላል። ይህም ሰነድ ስለ ሄሜስፊር ውሂብ ጎታ (ታሪካዊ የስልክ ጥሪ መዝገብ ውሂብ ጎታ) እና የሚያስተዳድሩት ሰዎች የአደዋወል ዘይቤ ተመሳሳይነትን በመከተል ጊዜያዊ ስልኮችን ስለሚያገናኙበት ገጽታ ይገልጻል። ሰነዱ ጊዜያዊ ስልኮችን “ድሮፕድ ወይም የተጣሉ ስልኮች” ይላቸዋል። ምክኒያቱም ተጠቃሚው አንዱን “ይጥል” እና ሌላ መጠቀም ስለሚጀምር ነው። ይህ ሲከሰት የተቀባይ ስልኮች ተመሳሳይ እስከሆኑ ድረስ የውሂብ ጎታ ስልተ ቀመራዊ (database analytics algorithms) ትንተና በአንዱ ስልክ እና በሌላኛው ስልክ ያለውን ግንኙነት መመርመር ይችላል።

እንኚህ እውነታዎች አንድ ላይ ሲጠቃለሉ የሚገግሩን፤ በርነር ወይም ጊዜያዊ ስልኮችን በጠቀም ከመንግስት ስለላ ለማምለጥ የሚደረግ ሙከራ በትንሹ ሲም ካርድን ወይም የስልክ ቀፎን ደግሞ አለመጠቀም፣ ሁለት የተለያዩ ቀፎዎችን በተመሳሳይ ግዜ አለመያዝ፣ በቀፎዎች እና በሚጠቀሙበት ስፍራ ግንኙነት እንዳይኖር መጠንቀቅ እንዲሁም በተመሳሳይ ሰዎች የሚደረግን የስልክ ጥሬ አለመቀበል ወይም አለመደወል አስፈላጊ መሆኑን ነው ። እነዚህ ዝርዝሮች የተሟሉ ናቸው ማለት አይደለም። ለምሳሌ ስልኩ በተሸጠበት ወይም ጥቅም ላይ በዋለበት ስፍራ በጆሮ ጠቢዎች አማካኝነት የሚደርግን አካላዊ ስለላን ወይም የደዋዮችን ድምጽ በቀጥታ ለመለየት በሚያስችል ሶፍትዌር የሚደረግን ስለላን አላካተትንም።

የGPS ማስታወሻ anchor link

GPS ወይም ሉላዊ የአቅጣጫ ስርዓት በአለም የትም ቦታ ላይ ያሉ መሳሪያዎች ያሉበትን ስፍራ በፍጥነት እና በትክክል እንዲያውቁ ያስችላል። GPS የሚሰራው ከሳተላይት የሚመጡ ሲግናሎችን በመተንተን ነው። እነዚህ ሳተላይቶች በአሜሪካ መንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ የህዝብ መገልገያዎች ናቸው። በብዛት ሰዎች ባለመረዳት እነኚህ ሳተላይቶች የGPS ተጠቃሚዎችን የሚያዩ ወይም GPS ተጠቃሚው የት እንዳለ የሚያውቁ ይመስላቸዋል። እውነታው ግን የGPS ሳተላይቶች ሲግናል ብቻ የሚያስተላልፉ ሲሆኑ ሳተላይቶቹ ምንም ዓይነት መረጃ ከስልኮት አያዩም ወይም አይቀበሉም። በተጨማሪም የሳተላይት እና የGPS ስርዓት ሰራተኞችም አንድ ተጠቃሚ ወይም መሳሪያ የት ስፍራ እንዳለ ወይም ስርዓቱን ምን ያህል ሰዎች እየተጠቀሙት እንዳለ አያውቁም።

ይህም የሚሆንበት ምክንያት እያንዳንዱ የGPS ሲግናል ተቀባይዮች (ልክ በስማርት ስልኮች ውስጥ እንዳለው) ያሉበትን ሥፍራ የሚያሰሉት ከተለያዩ ሳተላይቶች የሚመጡ ራዲዮ ሲግናሎችን ለመቀበል የፈጀባቸውን ጊዜ በመወሰን በመሆኑ ነው።

ታዲያ ስለ “GPS ክትትል” ስለምን እናወራለን? አብዛኛውን ጊዜ ይህ ክትትል የሚካሄደው የስማርት ስልኮች ውስጥ በሚገኙ መተግበሪያዎች አማካኝነት ነው። የስልኩን ስርዓተ ክወና ስላለበት ሥፍራ (በGPS አማካኝነት የተወሰነውን) ይጠይቃሉ። ከዛም በመቀጠል መተግበሪያዎቹ ኢንተርኔትን በመጠቀም ይህንን መረጃ ለሌላ ሰው ማስተላለፍ ይችላሉ። በተጨማሪም ትናንሽ የGPS ሲግናል ተቀባይ መሳሪያዎች ሊከታተሏቸው በሚፈልጉት ሰዎች ላይ በድብቅ ሊያደርጉባቸው ወይም ከተሽከርካሪዎች ጋር ተሰክተው ሊኖሩ ይችላሉ። እነኚህ የሲግናል ተቀባዮች ያሉበትን ሥፍራ በመወሰን በንቃት አውታረ መረብን (በብዛት የተንቀሳቃሽ ስልክ አውታረ መረብን) በመጠቀም መረጃውን ያስተላልፋሉ።

የተንቀሻቃሽ ስልክ ግንኙነቶችን መሰለል anchor link

የተንቀሳቃሽ ስልክ አውታረ መረቦች ቀድሞውኑ የተሰሩት የተጠቃሚዎችን የስልክ ጥሪ ሦስተኛ ወገን እንዳያደምጥ ተደርገው አይደለም። ይህ ማለት ትክክለኛ የራዲዮ ሲግናል ተቀባይ ያለው ማንኛውም ሰው የሌላን ሰው የስልክ ጥሪ ማዳመጥ ይችላል።

ምናልባት አሁን ባለንበት ጊዜ ሁኔታው የተሻለ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እንጂ ሙሉ በሙሉ የተቀረፈ አይደለም። የማመስጠሪያ ቴክኖሎጂዎች ሶስተኛ ወገን የስልክ ጥሪዎችን እንዳያደምጡ ለመከላከል በመደበኛ የተንቀሳቃሽ ስልኮች ላይ የተጨመሩ ናቸው። ነገር ግን አብዛኞቹ ቴክኖሎጂዎች የተሰሩት ደካማ በሆነ መንገድ ነው። (ጠንካራ ማመስጠሪያ እንዳይጠቀሙ አንዳንድ ጊዜ ጫናው ከመንግስትም ይሆናል)። በተጨማሪም ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉት በተዘበራረቀ ሁኔታ ነው። ስለዚህ በአንዳንድ የተንቀሳቃሽ ስልክ አግልግሎት ሰጪዎች ላይ ብቻ ይገኛል። በሌሎች ላይ ግን አይገኝም።፡ወይም በአንዳንድ አገሮች ላይ ይገኛል። በሌሎች ፈጽሞ አይኖርም። ወይም ደግሞ አንዳንድ ጊዜ እየተተገበሩ ያለው በትክክለኛው መንገድ ላይሆን ይችላል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ደግሞ የማመስጠሪያ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደ ሕግወጥነት ይቆጠራል። በአንዳንድ አገራት የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት ሰጪዎቹ ማመስጠሪያን ጨርሶ አያስችሉም ወይም ያረጁ መደበኛ ቴክኒኮችን ይጠቀማሉ። ይህ ማለት ትክክለኛ የራዲዎ ሲግናል ተቀባይ ያለው ማንኛውም ግለሰብ የስልክ ጥሪዎች እና አጭር የጽሁፍ መልዕክቶች በአየር ላይ በሚተላልፉበት ወቅት ጠልፎ መስማት እና ማንበብ ይችላል።

ከዚህ በተጨማሪም በአንዳንድ አገራት እና የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት ሰጪዎች እንደሚስተዋለው በኢንደስትሪው አሉ የሚባሉ ቴክኖሎጂዎችን ቢጠቀሙ እንኳን እስካሁን ድረስ የስልክ ጥሪዎችን መስማት የሚችሉ ሰዎች አሉ። በትንሹ የተንቃሳቃሽ ስልክ አገልግሎት ሰጪዎች የሰዎችን የስልክ ጥሪ መጥለፍ እና ማን እንደደወለ ወይም የአጭር ጽሁፍ መልእክት ማን እንደላከ፣ መቼ እንደላከ እና ምን እንዳሉ የመሳሰሉትን መረጃዎች መቅረጽ ይችላሉ። ይህ መረጃ ለአገር ውስጥ እና ለውጭ መንግስት መደበኛ ወይም ኢመደበኛ በሆነ መንገድ ሊሰጥ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ የውጭ መንግስታት የስልክ አግልግሎት ሰጪዎችን ስርዓት በመመዝበር/ሰርጎ በመገባት በድብቅ የተጠቃሚዎችን መረጃ ማግኘት የቻሉበት አጋጣሚ አለ። በተጨማሪም ከላይ እንደተገለጸው የIMSI ጠላፊ ወይም ካቸር በአቅራቢያዎ ባለ ማንኛውም ሰው ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። ይህም ስልክዎን በማሳሳት የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት ሰጪዎትን ሕጋዊ መሠረተ ልማት በመጠቀም ፋንታ የነሱን የሐሰተኛ “ምሰሶ” እንዲጠቀም በማድረግ የIMSI ካቸሩን የሚቆጣጠረው ሰው የእርስዎን ግንኙነት ሊጠልፍ ይችላል።

ራስን ሙሉ በሙሉ ከስለላ ለመከላከል የስልክ ጥሪዎች እና አጭር የጽሁፍ መልእክቶች በምንም መልኩ በሶስተኛ ወገን ከመደመጥ ወይም ከመቀዳት እንደማያመልጡ ማወቅ ነው። ምንም እንኳን የቴክኒካዊ ደረጃ ጥልቀቱ ከሀገር ሀገር፣ ከቦታ ቦታ ወይም ከስርዓት ስርዓት ቢለያይም በቴክኒክ ራስን ለመከላከል መሞከር በብዛት ደካማ እና በብዙ ሁኔታዎች ሊታለፍ የሚችል ነው። ደህንነቱ በተሻለ ሁኔታ እንዴት የጽሁፍ መልዕክት መላክ እና ማውራት እንደሚቻል ለመማር ከሌሎች ጋር ስለሚደረግ ግንኙነት የሚለውን ይመልከቱ።

ግንኙነት የሚያደርጉት ደህንነቱ የተጠበቀ የግንኙነት መተግበሪያዎችን በመጠቀም ከሆነ (የጽሁፍ ወይም የድምጽ ግንኙነት ሊሆን ይችላል) ይህ ሁኔታ የተለየ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም እነዚህ መተግበሪያዎች ግንኙነትዎን በማመስጠር ሊከላከሉልዎት ይችላሉ። ይህ ምስጠራ ጠንካራ ሊሆን እና ትርጉም ያለው ጥበቃዎችን ሊሰጥ ይችላል። ለግንኙነትዎ ደህንነቱ የተጠበቀ የግንኙነት መተግበሪያን በመጠቀም ሊያገኙት የሚችሉት የጥበቃ መጠን በሚጠቀሙት መተግበሪያ እና በመተግበሪያው አስራር ላይ ይመሰረታል። አንድ ወሳኝ ጥያቄ የሚሆነው የግንኙነት መተግበሪያው ግንኙነትዎን ለመከላከል ከዳር እስከ ዳር ማመስጠሪያን ይጠቀማል ወይስ አይጠቀምም የሚለው እና መተግበሪያውን የሰራው ወይም ያበለጸገው ሚስጥራዊነቱን መቀልበስ ወይም ማለፍ ይችላል ወይስ አይችልም የሚለው ነው።

ስልኮችን በሸረኛ ሶፍትዌሮች መበከል anchor link

ስልኮች በቫይረስ እና በማልዌር (ወይም በሸረኛ ሶፍትዌሮች) ሊበከሉ ይችላሉ። ይህም የሚሆነው ተጠቃሚዎች ተታለው በስልኮቻቸው ላይ ሸረኛ ስፍትዌሮችን ሳያውቁ ጭነው ወይም በስልኩ ሶፍትዌር ላይ ያሉ የደህንነት ህጸጾችን በመጠቀም አንድ ሰው ስልኩ ውስጥ ሰርጎ መግባት ችሎ ሊሆን ይችላል። እንደሌሎች የኮምፒውተር መሳሪያዎች ሁሉ ሸረኛ ሶፍትዌሮች በስልክ ተጠቃሚዎች ላይ ስለላን ሊያካሂዱ ይችላሉ።

ለምሳሌ በተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ ያለ ሸረኛ ሶፍትዌር በመሳሪያው ላይ ያሉ የግል ውሂቦችን (እንደ ተጠራቀሙ አጭር የጽሁፍ መልእክቶች እና ፎቶዎች) ሊያነብ ይችላል። በተጨማሪም የመሳሪያውን ሴንሰሮች ማለትም ማይክሮፎኖች፣ ካሜራ፣ GPS የመሳሰሉትን በመቀስቀስ ስልኩ የት ቦታ እንደሚገኝ ወይም አካባቢውን ለመቆጣጠር ግልጋሎት ሊውል፣ ወይም ስልኩን ራሱን ወደ ህጸጽነት ሊቀይሩት ይችላሉ።

ይህ ዘዴ በአንዳንድ መንግስታት በራሳቸው ስልክ አማካኝነት ሰዎችን ለመሰለል በተግባር ላይ ውሏል። ይህም ሰዎች የተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ባሉበት ክፍል ውስጥ ስሱ የሆኑ ውይይቶችን ሲያደርጉ በፍርሃት እንዲሆን አድርጓል። ለዚህም አንዳንድ ሰዎች ስሱ የሆኑ ውይይቶችን ሲያካሂዱ ስልኮቻቸውን ሌላ ክፍል ውስጥ በመተው ወይም የስልኩን ሃይል ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ጥንቃቄን እንዲወስዱ አድርጓል። አብዛኛውን ጊዜ መንግስታት ራሳቸው ሰዎች፣ አንዳንዴም የመንግስት ሰራተኞች ደህንነቱ ወደተጠበቀ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሲመጡ ስልኮቻቸውን ይዘው እንደይመጡ የሚከለክሉት ለዚህ ነው። ይህም በዋናነት ስልኮች በሸረኛ ሶፍትዌሮች ተበክለው ውይይቶችን ሊቀዱ እንደሚችሉ በመገንዘብ ነው።

በሐልዮት ደረጃ ቢሆንም ሌላው አሳሳቢ ነገር አንዳንድ ሸረኛ ሶፍትዌሮች ስልኩን በሚያጠፉበት ወቅት የጠፉ አስመስለው ሊያሳዩ እና በድበቅ ስልኩ እንደበራ እንዲቆይ ሊያደርጉ ይችላሉ (ጥቁር ስክሪን ያሳያሉ ስለዚህ ተጠቃሚዎች ይህንን አይተው ስልኩ እንደጠፋ በስህተት ያምናሉ)። ይህም አንዳንድ ሰዎች በጣም ስሱ የሆኑ ውይይቶችን በሚያደርጉበት ወቅት የስልኮቻቸውን ባትሪ በማውጣት እንዲሆን አስገድዷቸዋል።

ከላይ እንደተመለከትነው የስልኮችን ኃይል ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ላይ የተመሰረተ ጥንቃቄ በስልክ አገልግሎት ሰጪው ሊስተዋል ይችላል። ለምሳሌ አስር ሰዎች በአንድ ሕንጻ ውስጥ ቢገኙ እና በተመሳሳይ ሰዓት ስልኮቻቸውን ቢያጠፉ የስልክ አገልግሎት ሰጪው ወይም እንደዚህ ያሉ ክትትሎችን የሚያደርግ ሌላ አካል እነዚህ ሰዎች በተመሳሳይ ቦታ ሚስጥራዊ ስብሰባን እያካሄዱ እንደሆነ ድምዳሜ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ። ነገር ግን የስብሰባው ተሳታፊዎች ስልኮቻቸውን በቤቶቻቸው ወይም በቢሮዎቻቸው ትተውት ቢሄዱ ይህን ለመጠርጠር አዳጋች ይሆናል።

በተያዙ ስልኮች ላይ የሚደረግ የአባዲና ምርመራ anchor link

እጅግ በጣም ያደገ እና የተደራጀ በተንቀሳቃሽ ስልኮች ላይ የአባዲና ምርመራ የሚያካሂድ ስርዓት አለ። አንድ ተንታኝ ባለሙያ በቁጥጥር ስር የገባን ስልክ ከልዩ መሳሪያ ጋር በማገናኘት በስልኩ ውስጥ የተጠራቀሙ ውሂቦችን ማለትም በፊት የተደረጉ እንቅስቃሴዎችን፣ የስልክ ጥሪዎችን እና አጭር የጽሁፍ መልዕክቶችን ማንበብ ይችላል። ይህ የአባዲና ምርመራ ተጠቃሚዎች ሊያገኟቸው ወይም ሊያዩቸው የማይችሉ፤ ለምሳሌ ያህል የጠፉ አጭር የጽሑፍ መልዕክቶችን መልሶ ሊያገኝ ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ የአባዲና ምርመራ ቀላል የሆኑ የስክሪን ቁልፎችን ማለፍ ይችላል።

በተወሰኑ ውሂቦች እና መዝገቦች ላይ የአባዲና ምርመራ እንዳይካሄድ የሚያሰናክሉ ወይም የሚከላከሉ ወይም ውሂቦችን በማመስጠር በአባዲና መርማሪው እንዳይነበቡ የሚያደርጉ በርካታ የስማርት ስልክ መተግበሪያዎች እና ሶፍትዌሮች አሉ። በተጨማሪም ራቅ ካለ ስፍራ በስልኩ ባለቤት ወይም ይህን እንዲያደርግ የስልኩ ባለቤት ሃላፊነት በሰጠው ግለሰብ በስልኩ ላይ ያሉ ውሂቦች ሙሉ በሙሉ ተጠርገው እንዲጠፉ የሚያደርጉ ሶፍትዌሮች አሉ።

እነኚህ ሶፍትዌሮች ስልክዎ በወንጀለኛ ቁጥጥር ስር ከገባ በስልኩ ላይ ያለው ውሂብ በወንጀለኛው እንዳይገኝ ለመከላከል ይጠቅማል። ነገር ግን በቁጥጥር ስር በዋሉ ስልኮች ላይ ሆን ብሎ ማስረጃን ማጥፋት ወይም ምርመራን ማሰናከል በተለየ ወንጀለኝነት አስጠይቆ የከፋ አደጋ ሊያመጣ ይችላል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ መንግስታት በዜጎቻቸው የተከሰሱበትን ወንጀል የከፋ ቅጣት ለማስቀጣት ይህንን ይጠቀሙበታል።

የስልኮች አጠቃቀም ጠባይ የኮምፒውተር ትንተና anchor link

መንግሥታት ኮምፒውተርን በመጠቀም የብዙ የስልክ ተጠቃሚዎችን የስልክ ውሂብ አጠቃቀም ላይ ያለውን ስርዓት ለማግኘት ፍላጎት አሳይተዋል። እነኚህ የአጠቃቀም ስርዓት ትንተናዎች ዜጎች ባልተለመደ መልኩ ስልኮቻቸውን ሲጠቀሙ ለምሳሌ ግላዊነታቸውን ለመጠበቅ የሚያደርጉትን ጥንቃቄ የመንግስት ባለሞያዎች እንዲያውቁ ሊጠቅሙ ይችላሉ።

ከውሂብ ትንተናው መንግስታት ለማወቅ ከሚተጋባቸው ነገሮች ውስጥ የሚከተሉት ምሳሌዎች ይገኙበታል፦ ሰዎች እርስ በእርስ እንደሚተዋወቁ እና እንደማይተዋወቁ ለማወቅ፣ አንድ ሰው ብዙ ስልኮችን እንደሚጠቀም ወይም ስልኮችን እንደሚቀያይር ለመመርመር፣ ሰዎች በቡድን ሆነው አንድ ላይ መጓዛቸውን ወይም በብዛት እርስ በእርስ መገናኘታቸውን ለመመርመር፣ ሰዎች በቡድን ሆነው ስልኮቻቸውን ባልተለመደ ወይም በሚያጠራጥር መንገድ መጠቀማቸውን ለመመርመር፣ የጋዜጠኛ ሚስጥራዊ የመረጃ ምንጮችን ለመለየት ናቸው።