Surveillance
Self-Defense

ለማክ OS X የPGP አጠቃቀም

በአሁን ሰዓት በስርዓቱ ላይ ባጋጠሙ ተጋላጭነቶች ምክንያት ኢኤፍኤፍ PGPን እንዲጠቀሙ አይመክርም፡፡ ለተጨማሪ መረጃ ጦማራችንን ማንበብ ይችላሉ፡፡ ሌሎች አማራጭ ከጥግ እስከ ጥግ የተመሰጠሩ አገልግሎቶችን ማግኘትም ይችላሉ፡፡ የትኛው ለእርስዎ እጅግ ምርጡ እንደሆነ እርግጠኛ ካልሆኑ ሲግናል ለአንድሮይድ እና ሲግናል ለአይኦኤስን በመጠቀም እንዲጀምሩ እንጠቁማለን፡፡

በአሁን ሰዓት በስርዓቱ ላይ ባጋጠሙ ተጋላጭነቶች ምክንያት ኢኤፍኤፍ PGPን እንዲጠቀሙ አይመክርም፡፡ ለተጨማሪ መረጃ ጦማራችንን ማንበብ ይችላሉ፡፡ ሌሎች አማራጭ ከጥግ እስከ ጥግ የተመሰጠሩ አገልግሎቶችን ማግኘትም ይችላሉ፡፡ የትኛው ለእርስዎ እጅግ ምርጡ እንደሆነ እርግጠኛ ካልሆኑ ሲግናል ለአንድሮይድ እና ሲግናል ለአይኦኤስን በመጠቀም እንዲጀምሩ እንጠቁማለን፡፡

Last reviewed: 
2018-05-12
ይህ ገጽ ከእንግሊዘኛው ቅጂ የተተረጎመ ነው፡፡ የእንግሊዘኛው ቅጂ ምን አልባት የበለጠ የዘመነ ይሆናል፡፡

እጅግ የተሳካለት ግለሚስጥር ወይም ፕሪቲ ጉድ ፕራይቬሲ (PGP) የተባለው የኢሜል ግንኙነትዎ ከታቀደለት ተቀባይ ግለሰብ በስተቀር በሦስተኛ አካል እንዳይነበብ የሚከላከል ስርዓት ነው። በተጨማሪም ኮምፒውተርዎ ቢሰረቅ ወይም ቢሰበር በኮምፒተርዎ ላይ የተጠራቀሙት ኢሜሎችዎ እንዳይመዘበሩ ይከላከላል።

ከአንድ ግለሰብ የተላከልዎት ኢሜል በትክክል ከሚያውቁት ግለሰብ ወይም ከሦስተኛ አካል የተላከ የሀሰት መልዕክት መኾኑን ወይም አለመኾኑን ለማረጋገጥ ሊያገለግል ይችላል (ይህ ካልኾነ እውነተኛ የሚመስል ኢሜል በቀላሉ ሊፈጠር ይችላል)። ለስለላ እና የማሳሳት ዘመቻ ዒላማ የሚኾኑ ከኾነ እነዚህ ሁለቱም በጣም አስፈላጊ መከላከያ ናቸው።

PGPን ለመጠቀም አሁን ከሚጠቀሙበት የኢሜል ፕሮግራም ጋር አብረው የሚሠሩ ተጨማሪ ሶፍትዌሮችን መጫን ይጠበቅብዎታል። በተጨማሪም በግልዎ የሚይዙት የግል ቁልፍ መፍጠር አለብዎት። ይህ የግል ቁልፍ የተላከልዎትን ሚስጥራዊ ኢሜል ለመፍታት እንዲሁም የሚልኳቸውንም በእርግጥም እርሶ እንደላኳቸው ለማሳየት የዲጂታል ፊርማ ለመፈረም የሚጠቀሙበት ነው። በመጨረሻም የአደባባይ ቁልፍዎን እንዴት እንደሚያጋሩ ይማራሉ። የአደባባይ ቁልፍ ሌሎች ሰዎች ለእርስዎ ሚስጥራዊ ኢሜልን ከመላካቸው በፊት ሊያውቁት የሚገባ እና እርሶ የሚልኩትንም እንዲሁ የሚያረጋግጡበት ቅንጣቢ መረጃ ነው።

ይህ መመሪያ የማክን አብሮገነብ ሜል (built-in Mail) ፕሮግራም ወይም አማራጭ ዝነኛ የኢሜል ፕሮግራም በኾነው በሞዚላ ተንደርበርድ PGPን በአፕል ማክ (በአይፓድ ወይም አይፎን አይደለም) ላይ እንዴት እንደሚጠቀሙ ያሳይዎታል።

እንደ ጂሜል፣ ሆትሜል፣ ያሁ! ሜል ወይም አውትሉክ ላይቨ ባሉት የድር ኢሜል አገልግሎት ላይ PGPን በቀጥታ መጠቀም አይችሉም። ይኹንና የዌብሜል እድራሻዎን በኮምፒውተርዎ ላይ ካለው ዌብሜይል ወይም ከተንደርበርድ ፕሮግራም ጋር በማዋቀር መጠቀም ይችላሉ።

ያስተውሉ ይህ እንዲሠራ በሁለቱም የኢሜል ልውውጥ ዳር ያሉ ሰዎች ከPGP ጋር ተኳኋኝ የኾነ ሶፍትዌር መጠቀም ይኖርባቸዋል።

በመደበኛነት ግለሰቦች ይህን የሚጠቀሙት ከማንኛውም ግለሰብ ጋር በማይጋሩት የራሳቸው ግላዊ መሣሪያዎች ላይ ነው። ጥሩነቱ PGP ለብዙ ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮች እና ተንቀሳቃሽ ስልኮች ተኳኋኝ ኾኖ ይገኛል። የራሳቸውን ስሪት እንዲያዋቅሩ እንዲረዳቸው ይህንን መመሪያ ይጠቁሟቸው። ይህ መመሪያ ለማክ ተጠቃሚዎች የሚያገለግል ነው።

 

በማክ ኮምፒውተርዎ ላይ የGPG መሳሪያዎችን መጫን Anchor link

PGP ከአንድ በላይ የኾኑ ሶፍትዌሮች እንዲጠቀሙበት ተደርጎ የተፈጠረ ተኳኋኝ ሶፍትዌር ነው። ለPGP የምንጠቀመው ሶፍትዌር ከGPG መሳሪያዎች በማክ ኮምፒውተሮች ላይ የሚሠራውን GPG ስዩት በመባል የሚታወቀውን አንዱን ስንጥር ነው። ይህም ሶፍትዌር ማንኛውም ሰው እንዲጠቀመው ከክፍያ ነጻ የኾነ ምንጨ-ክፍት ነው። ይህ ማለት ማንኛውም ግለሰብ ህጸጹን እና መምጫውን ለማጣራት ሶፍትዌሩ የተሠራበትን ምንጨ-ኮድ ማግኘት ይችላል።

አንዴ የGPG ስዩት ከተጫነ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ቁልፍዎን ማዋቀር፤ በመቀጠልም PGPን በአፕል ሜል እና በአማራጭነት በተንደርበርድ እንዲተገበር ማድረግ ይችላሉ።

አንደኛ ደረጃ፦ ፕሮግራሙን ይጫኑ።

በመጀመሪያ በድር መዳሰሻዎ ወደዚህ ገጽ ይሂዱ https://www.gpgtools.org/ እና “ዳውንሎድ GPG ስዩት” የሚለውን ይምረጡ።

ጠቅ በማድረግ ሶፍትዌሩን ለመጫን የሚያችልዎትን የዲስክ ኢሜጅን ያገኛሉ። በኮምፒውተርዎ ላይ የሦስተኛ ወገን ሶፍትዌር የመጫን ልምድ ከሌለዎት በአቅራቢያዎ የሚገኝ የማክ አዋቂን ይጠይቁ። የቴክኖሎጂ ባለሞያዎቹ ስለ PGP ወይም ምስጢራዊነት ምንም ዕውቀት ባይኖራቸው እንኳ እርስዎን ለማገዝ አያዳግታቸውም።

ኢንስቶል የሚለውን ጠቅ ማድረግ በኮምፒውተርዎ ላይ የሚጨመሩትን መሣሪያዎች ዝርዝር ይሰጥዎታል።

እየጫንኩ ያለሁት ነገር በትክክል ምንድን ነው?

እነዚህ አጋዥ መሣሪያዎች በማክ ኮምፒውተርዎ ከአንድ በላይ የኾኑ ፕሮግራሞች PGPን መጠቀም እዲችሉ አብዛኛውን ጊዜ ከመጋረጃ በስተጀርባ የሚሠሩ ናቸው። እነዚህንም በቀጥታ ከሚጠቀሟቸው መተግበሪያዎች ይልቅ ሌሎች ፕሮግራሞች መጠቀም የሚችሏቸው ፕሮግራሞች እንደኾኑ ያስቧቸው። GPGሜል የተባለው አፕል ሜል የPGP ኢሜልን እንዲልክ እና እንዲያነብ ያደርጋል። GPG ኪይቼን አክሰስ የተባለው በማክዎ ላይ ሌሎች የማለፊያ ቃላትዎን በሚያስቀምጡበት ተመሳሳይ ስርዓት የግል እና የአደባባይ ቁልፎችዎን ያኖርልዎታል። GPG ሰርቪስ ከኢሜል ሌላ ፕሮግራሞች (ለምሳሌ ወርድ ፕሮሰሰር ) ላይ PGPን መጠቀም የሚያስችልዎት በOS X ላይ በምርጫ የኾነ ገጽታ ይጨምርልዎታል። GPGፕሪፈረንስ በአፕል ምርጫ ላይ የPGPን መዋቅር እንዲቀይሩ ያደርጋል። በመጨረሻም ማክGPG2 የተባለው ደግሞ ማንኛውም ፕሮግራም ሚስጥራዊነትን ወይም ፊርማን እንዲከውን የሚያግዝ መሰረታዊ መሣሪያ ነው።

በጥቅምት 2007 የGPG መሣሪያዎች ቡድን እንዳስታወቀው GPGን ከአፕል ሜል መተገበሪያ ጋር እንዲጠቀሙ የሚረዳዎትን እና ከጥቅሎቻቸው አንዱ ክፍል የኾነውን GPGሜል በቅርቡ እንደሚቀይር አስታውቋል።  ይህ አጋዥ ስልጠና GPGን ከተንደርበርድ ጋር ስለመጠቀም ስለኾነ እነዚህን ምንዝሮችን አይጠቀምም።.  የGPG ስዩትን ክፍል የኾነውን ዚሮ-ኮስት መጠቀም ይችላሉ።  በተጨማሪም እነዚህ አጋዥ መሳሪያዎች ሁሉም “ነጻ ሶፍትዌር” ስለኾኑ በነጻ ሶፍትዌር መንፈስ GPGሜል የተሳራበትን ምንጭ ኮድ በነጻነት መመርመር፣ ማስተካከል እና ማከፋፈል ይችላሉ።  ለተጨማሪ መረጃ ውሳኔያቸውን በተመለከት የGPG ቱልስ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እና መልሶቻቸው ይመልከቱ።

GPG ስዩትን ለመጫን “ኮንቲኒው” የሚለውን ጠቅ ያድርጉ።

የመጫን ሂደቱ እንደተጠናቀቀ የGPG ኪይቼን (የቁልፍ ማህደር) በቀጥታ ተከፍቶ የPGP ቁልፍዎን እንዲያመርቱ ይጠይቅዎታል። ይህ ካልኾነ ግን ወደ ትግበራ ማህደር ሄደው ይክፈቱት።  የPGP ቁልፍዎን ለመፍጠር “ኒው” የሚለውን ጠቅ ያድርጉ።

አሁን የግል እና ይፋዊ ቁልፎች መፍጠር ይጀምራሉ፡፡ የአደባባይ ቁልፎች ስነ መሰውር እና PGP መግቢያ የተሰኘው መመሪያችን ላይ ስለቁልፎች ምንነት ለመረዳት የተጻፈውን ያንብቡ፡፡

ሁለተኛ ደረጃ፦ የPGP ቁልፍዎን መፍጠር

አንዳንድ ጊዜ አዲስ ሶፍትዌርን ሲጭኑ ኮምፒውተርዎ እንዴት መመለስ እንዳለብዎት ምክር ሳይሰጥ ግልጽ የኾነ መልስ በሌላቸው ጥያቄዎች ይነዘንዝዎታል። ይህ ያንን ያሚያስታውሱበት ጊዜ ነው።

አፍታ ወስደው ምን መልስ እንደሚሰጡ ይመከራሉ። ምክንያቱም ዘግይቶ የPGP ቁልፍዎን ዝርዝር መቀየር ከባድ ሊኾን ስለሚችል እና ቁልፍዎን የኾነ ቦታ እንዲታተም ከመረጡ በኋላ እትሙን መቀልበስ ስለማይችሉ ነው። (በሺዎች የሚቆጠሩ እየተንሳፈፉ ያሉ የ1990 አሮጌ ተጣማሪ ቁልፎች ከፈጠሯቸው ሰዎች ስም እና አሮጌ ኢሜል አድራሻ ጋር አሉ።)

የPGP ቁልፎች ቁልፉን ከእርሶ ጋር የሚያያይዙ ስም እና የኢሜል አድራሻ ይይዛሉ። የኢሜል አድራሻው ሌሎች ግለሰቦች ለእርስዎ መልዕክት ሲያመሰጥሩ የትኛውን ቁልፍ መጠቀም እንዳለባቸው የሚያውቁበት አንዱ መንገድ ነው።

መቼ ነው እውነተኛ ስሜን እና የኢሜል አድራሻዬን በPGP ቁልፌ ላይ መጠቀም የሌለብኝ? ቁልፌን መጫን የሌለብኝስ መቼ ነው?

ብዙ ተጠቃሚዎች እውነተኛ የኢሜል አድራሻን በቁልፍዎ ላይ መጨመርዎ እንዲሁም እርስዎን ከትክክለኛው ቁልፍ ጋር የሚያዛምዱበትን ተጣማሪ ቁልፍ አገልጋይ ላይ መጫን ትርጉም ይሰጣቸዋል። በቀጥታ የኢሜል መልዕክት ሊሰዱልዎ ከዛም አልፎ በትክክለኛው ቁልፍ የተሰወረ መኾኑን ማወቅ ይችላሉ። የተፈረመበት ኢሜል ከእርስዎ ሲቀበሉም የዲጂታል ፊርማው የስምዎ ምልክት ያለበት ይኾናል።

ይኹንና ለአንዳንድ ሰዎች እውነተኛ ስማቸውን በቁልፋቸው ላይ ማኖር ትርጉም አይሰጣቸውም። ለምሳሌ የስጋት ሞዴልዎ የእርሶን ማንነት (እና የኢሜል አድራሻዎን) ከቁልፎ ጋር መያያዝን የሚጨምር ከኾነ ይህ መልካም ሃሳብ አይደለም። ኤድዋርድ ስኖውደን ማንነቱን ከመገለጡ በፊት ከጋዜጠኞች ጋር ሲገናኝ የነበረው PGP እና ስምአልባ የኢሜል አድራሻን በመጠቀም ሲኾን የPGP ቁልፉም በእርግጠኝነት የስሙ ምልክት አልነበረውም።

ቁልፍዎን መጫን የተለመደ ተግባር ነው። ይኹንና የራስዎን ስም ባይጠቀሙም እንኳ ምስጢራዊነትን እንደሚጠቀሙ ሊያጋልጥ ይችላል። በተጨማሪም እንደምናየው ሌሎች ሰዎች የእርሶን ቁልፍ ይጭኑና ከራሳቸው ቁልፍ ጋር ሊያዛምዱት ይችላሉ። ይህም ከእርሶ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ሊያሳይ ይችላል። ይህንን ግንኙነት ሰዎች እንዲያውቁት የማይፈልጉ ከኾነ ጉዳት ሊያመጣብዎ ይችላል። ምናልባትም ደግሞ ግንኙነት የሌለዎት ሊኾኑ ይችላሉ። አጥቂዎ ግን ሰዎች ዝምድና እንዳለዎት እንዲያስቡ የሚፈልግ ከኾነ አደገኛ ሊኾን ይችላል።

ምጥን መመሪያ ይኅውልዎ፦ በአጠቃላይ የተለየ የውል ስም ለመጠቀም የሚያስቡ ከኾነ ቁልፍዎን በሚፈጥሩበት ወቅት ያንን የውል ስም (እና ተለዋጭ ኢሜል) ይጠቀሙ። በጣም አደገኛ የኾነ አካባቢ የሚኖሩ ከኾነ ሰዎች በጭራሽ PGPን እንደሚጠቀሙ ወይም ከማን ጋር ግንኙነት እንደሚያደርጉ እንዳያውቁ የሚፈልጉ ከኾነ ቁልፍዎን በአደባባይ የቁልፍ አገልጋይ ላይ አይጫኑ። በተጨማሪም የሚያገኙት ቡድን ስብስብ የእርስዎን ቁልፍ መጫን እንደሌለበት ግንዛቤው እንዳለው ያረጋግጡ። የቁልፍዎን በተጣማሪ የቁልፍ አገልጋይ ላይ መገኘትን የማይጠይቁ ሌሎች የቁልፍ ማረጋገጫ መንገዶች አሉ። እነርሱንም ለማየት የቁልፍ ማረጋገጫን ይመልከቱ።

ሌሎች በቀላሉ ቁልፍዎን አግኝተው ሚስጥራዊ መልዕክት እንዲሉኩልዎ ከፈለጉ “አፕ ሎድ ፐሊክ ኪይ አፍተር ጀነሬሽን” የሚለውን ሳጥን ጠቅ ያድረጉ። ይህም ልክ የስልክ ቁጥርዎን በአደባባይ የስልክ መዝገብ ላይ እንደማኖር ነው። ለእርስዎ ባያስፈልግም ለሌሎች ግን ለአጠቃቀም ምቹ ነው።

ቁልፉን ከማምረትዎ በፊት “አድቫንስድ ኦፕሽንስ” የሚለውን ያስፉ። የአስተያያት መስጫውን ባዶውን ይተውት፣ በመቀጠልም የቁልፍ ዓይነቱን በነባሪው “RSA ኤንድ RSA (ዲፎልት)” እንደኾነ ይተውት። ነገር ግን የመጠን (ሌንግዝ) መስኩን ወደ 4096 መቀየርዎን ያረጋግጡ።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የቁልፍዎ የአገልግሎት ዘመን ያበቃል። ይህ በሚኾንበት ጊዜ ሌሎች ሰዎች ለእርሶ በሚልኳቸው አዳዲስ ኢሜልዎች ቁልፉን መጠቀም ያቆማሉ። ይህ ለምን እንደኾነ ማስጠንቀቂያ ወይም ማብራሪያ ላያገኙ ይችላሉ። ስለዚህ በቀን መቁጠሪያዎ ላይ ምልክት ማድረግ እና የቁልፉ አገልግሎት ዘመን ከሚያበቃበት ከወር ወይም ቀደም ብሎ ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት ይጠበቅብዎታል።

ነባሩን ቁልፍ አዲስ የወደፊት የአገልግሎት ዘመን ማብቂያ በመስጠት እና የእድሜ ዘመኑን በማራዘም ወይም ከመነሻው አዲስ ቁልፍን በመፍጠር ነባሩን ቁልፍ መቀየር ይቻላል። በሁለቱም ሂደቶች PGPን ተጠቅመው ኢሜል የሚልኩልዎትን ግለሰቦች ማግኘት እና የተቀየረውን ቁልፍ እጃቸው ማስገባታቸውን ማረጋገጥ ሊያስፈልግዎ ይችላል። የአሁን ሶፍትዌሮች በራስ ሰርነት እምብዛም አይደሉም። ስለዚህ ለራስዎ ማስታወሻ ያኑሩ። ይህን መተግበር የሚችሉ ካልመሰለዎት ደግሞ የቁልፉ የአገልግሎት ዘመን እንዳያበቃ አድርገው ማቀናበርን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይችላሉ። ይህን ካደረጉም ለወደፊቱ የግል ቁልፍዎ ቢጠፋብዎት ወይም PGPን መጠቀም ቢያቆሙ ከብዙ ጊዜ በኋላ ሌሎች ሰዎች ከእርስዎ ጋር ለመገናኘት ሊጠቀሙት ይችላሉ።

ዝግጁ ሲኾኑ “ጀነሬት ኪይ” የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ።

ኮምፒውተርዎ ሁለቱንም ማለትም የአደባባይ እና የግል ቁልፍዎን መፈብረክ ይጀምራል። ፈብርኮ ለመጨረስ ከጥቂት ደቂቃዎች በላይ መውሰድ የለበትም። (ጥቂት ጊዜን የሚወስደው ቁልፍዎን ለመፈብረክ ኮምፒውተርዎ የተለያዩ ቁጥሮችን ስለሚሰበስብ ነው። ይህንንም ኮምፒውተርዎ ባለ ስድስት ገጽ ጠጠርን (ዳይስ) እጅግ በጣም ብዙ ጊዜ ሲወረውር አድርገው አስቡት።)

ቁልፍዎን አምርተው ሲጨርሱ በGPG ኪይቼን አክሰስ (የቁልፍ ማኖሪያ ጎታ) ውስጥ ቁልፉ ተዘርዝሮ ያዩታል። በቁልፍዎ ላይ ሁለቴ ጠቅ በማድረግ የPGP ቁልፍዎን በልዩ መንገድ የሚለዩበትን “የጣት አሻራውን” ጨምሮ ማየት ይችላሉ። (ይህን ለማየት የቁልፍ ማረጋገጫ ይመልከቱ)።

አሁን የመሻሪያ ምስክር ወረቀት ለማተም መልካም ጊዜ ነው።

ወደፊት የግል ቁልፍዎ በሌላ ሰው እንደተቀዳ ጥርጣሬ የተሰማዎት ከኾነ በአጋጣሚ የግል ቁልፍዎን የሰረዙት ወይም የጣሉት እንደኾነ ወይም የይለፍ ሐረግዎን የረሱ እንደኾነ የመሻሪያ ምስክር ወረቀትን በመጠቀም ለሁሉም ሰው ቁልፉ የተሻረ ወይም የተሰረዘ መኾኑን መንገር ይችላሉ።

የመሻሪያ የምስክር ወረቀት ለማተም የግል ቁልፍ እና የይለፍ ሐረግ ሲለሚያስፈልግዎ አሁኑኑ አንድ መፍጠሩ የተሻለ ነው። በኋላ ለመፍጠር አስበው ችላ ካሉት ግን እንደኛውን ወይም ሌላኛውን ይጥሉትና ዘግይቶ መፍጠር አይችሉም። ስለዚህ የምስክር ወረቀቱን ለማተም ቁልፍዎ ላይ ጠቅ በማድረግ የ“ኪይ” መግቢያ ምናሌን በመቀጠልም “ክሬት ሪቮኬሽን ሰርትፊኬት”ን ይምረጡ። ሰነዱን እንዲያስቀምጡ የሚጠይቅ ይመጣልዎታል። የቁልፉን የመጠባበቂያ ቅጂ ማስቀመጥ ሊያስፈልግዎት ይችላል (የሚከተለውን ደረጃ ይመልከቱ)።

ሦስተኛ ደረጃ፦ የPGP ቁልፍዎን መጠባበቂያ ያስቀምጡ

የግል ቁልፍዎን መጠቀም የማይችሉ ከኾነ አዲስ የሚመጣልዎትን ማንኛውንም የPGP ሜል ወይም ድሮ የተላከልዎትን ኢሜሎች መፍታት እይችሉም። በሌላ በኩል ደግሞ የግል ቁልፍዎን ደህንነት በተቻልዎት አቅም መጠበቅ ይኖርብዎታል።

በጥንቃቄ በሚያስቀምጡት ፍላሽ ድራይቭ ላይ የቁልፍዎን ቅጂ ማስቀመጥ ሊያስፈልግዎት ይችላል። ይህም የሚያስፈልግዎት ዋና ቁልፍ ከጠፋብዎት ብቻ ቢኾንም ለደህንነትዎ ሲሉ አቅም ያላቸው አጥቂዎች እጅ እንዳይገባ መጠበቅ አለብዎት።

የPGP የግል ቁልፌ በአጥቂዎቼ ቁጥጥር ስር ገባ ማለት አጥቂዎቼ ሰነዶቼን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠሩት ማለት ነውን?

ማክዎ የተሰረቀ ወይም የመጠባበቂያ ቁልፍዎ ከእርሶ የተወሰደ ቢኾንስ? የPGP መልዕክትዎ ተጋላጭ ነው ማለት ነውን? አይደለም! ጠንካራ የማለፊያ ሐረግ ከመረጡ እና ምን እንደኾነ ሌሎች ማወቅ እስካልቻሉ ድረስ በአብዛኛው የተጠበቁ ነዎት። እርግጠኛ ለመኾን የድሮውን ቁልፍዎን መሻር እና አዲስ የPGP ቁልፍ መፍጠር ሊያስፍልግዎት ይችላል። ይህም የድሮ ቁልፍዎ ድሮ የተላኩልዎትን ኢሜሎችን መፍታት ባይከለክልም ሌሎች ስዎች አዲስ መልዕክቶችን ሲልኩልዎት የድሮውን ቁልፍ እንዳይጠቀሙ ግን ያደርጋል።

<

የቁልፍዎን ተጠባባቂ ለማኖር የGPG ኪይቼን ይክፈቱ። ቁልፍዎን ይምረጡ እና ከሰሪ አሞሌው “ኤክስፖርት” ላይ ጠቅ ያድርጉ። የፍላሽ ድራይቭዎን ኮምፒውተሩ ላይ ያገናኙት እና በ“ሴቭ አስ ... ” መገናኛ ውስጥ “ኸዌር” የሚለው ክፍል ላይ ይምረጡት። “አላው ሴክሬት ኪይ ኤክስፖርት” አመልካች ሳጥንን ያመልክቱ።

 

አፕል ሜልን ማዋቀር Anchor link

አፕል ሜልን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲከፍቱ የኢሜል አድራሻዎትን ማዋቀር የሚያስችልዎ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቻ የሚመጣ አዋቂ ያሳይዎታል። ስምዎን፣ የኢሜል አድራሻዎን እና የማለፊያ ቃልዎን ያስፍሩና ‘ክሬት’ የሚለውን ጠቅ ያድርጉ።

የሜል አድራሻን የማዋቀሪያ አዋቂ

እንደ ጂሜል ያለ ታዋቂ ነጻ የኢሜል አገልግሎትን የሚጠቀሙ ከኾነ ‘ኮንቲኒው’ የሚለውን ጠቅ ሲያደርጉ አፕል ሜል የኢሚልዎን ቅንብር በቀጥታ ማግኘት አለበት። ይህን ማድረግ ካልቻለ የIMAP እና የ SMTP ቅንብሩን በትዕዛዝ ማቀናበር ይኖርብዎታል። ለኢሜል የሚጠቀሙትን ኩባንያ ወይም የኢሜል አገልግሎት ሰጪዎን በደንብ የሚያውቅ እና ክህሎት ያለውን ሰው ይጠይቁ። (ይህም ከእርሶ ጋር አንድ ዓይነት የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪን (ISP) የሚጠቀም የመሥሪያ ቤትዎ የIT ሠራተኛ ወይም ሞያ ያለው ጓደኛዎ ሊኾን ይችላል። ስለ PGP ማወቅ አይጠበቅበትም ነገር ግን “የአፕል ሜሌን ልታዋቅርልኝ ትችላለህን?” ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ)።

የልብ አወቅ ሜል አድራሻ አወቃቀር

አዲስ መልዕክትን ሲያቀናብሩ ከርዕሰ ነገሩ መስክ በታች ሁለት አዶዎች አሉ። እነዚህም ኢሜሉን የሚያመሰጥሩበት የሰሌዳ ቁልፍ እና ዲጂታ የኢሜል ፊርማ የሚፈርሙበት የኮከብ ምልክት ናቸው። የሰሌዳ ቁልፉ የተቆለፈ ከኾነ ኢሜሉ ምስጢራዊ ይኾናል ማለት ሲኾን ኮከቡ ላይ ምልክት ካለበት ኢሜሉ የዲጂታል ፊርማ ይኖረዋል ማለት ነው።

 

በPGP የተፈረመ ወይም የተመሰጠረ ኢሜል መላክ Anchor link

የሚቀበለው ሰው የPGP ተጠቃሚ ባይኾንም እንኳን የሚልኩትን ኢሜል ሁልጊዜ መፈረም ይችላሉ። ለመጀመሪያ ጊዜ ኢሜል ሲፈርሙ የማለፊያ ሐረግዎን የሚጠይቅ ብቅ ባይ መስኮት ይከፈታል። ምክንያቱም ኢሜሎችን በዲጂታል መፈረም የምስጢርር ቁልፍ ስለሚያስፈልገው ነው።

ኢሜልን ማመስጠር የሚችሉት ኢሜሉን የሚልኩለት ሰው የPGP ተጠቃሚ ከኾነ እና የአደባባይ ቁልፉንም እጅዎ ካስገቡ ብቻ ነው። የማመስጠሪያው የሰሌዳ ቁልፍ አዶ ካልተቆለፈ እና አመድማ ከኾነ የተቀባዩን የአደባባይ ቁልፍ በመጀመሪያ ኢንፖርት ማድረግ አለብዎት ማለት ነው። ወይ እንዲልክልዎት ይጠይቁ’ አልያም ቁልፉን ከአደባባይ ቁልፍ አጋልጋይ ለማግኘት የGPG ኪይቼን አክሰስ መተግበሪያን ይጠቀሙ።

ፍጹም ደህንነቱን ለመጠበቅ ከቁልፍ አገልጋይ ወይም ከባልደረባዎ ያገኙትን ቁልፍ ማረጋገጥ አለብዎት። የቁልፍ ማረጋገጫ የሚለውን ክፍል ይመልከቱ።

 

PGPን ከሞዚላ ተንደርበርድ ጋር መጠቀም Anchor link

ይህ የሞዚላ ነጻ ምንጨ ኮድ የኾነውን ተንደርበርድ ሜል ደንበኛ እና የኤኒግሜል ተሰኪን ከGPG ጋር በመጠቀም ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የኢሜል ምስጠራን የሚያሳይ ነው።

በመጀመሪያ ተንደርበርድን ከዚህ ያውርዱ https://www.mozilla.org/thunderbird, በGPG ቱልስ እንዳደረጉት የዲስክ ኢሜጁን ቁብ አድርጉ እና ተንደርበርድን ስበው አፕሊኬሽንስ ማህደር ውስጥ ያስገቡት። ለመጀመሪያ ጊዜ ሲከፍቱት ነባሪ የኢሜል ደምበኛዎ ኾኖ እንዲቀመጥ እንደሚፈልጉ ይጠይቅዎታል። ይሂዱና “ሴት አስ ዲፎልት” የሚለውን ጠቅ ያድርጉ።

ከዚያም ለመጀመሪያ የተከፈተውን አዋቂ ያያሉ። ያልዎትን የኢሜል አድራሻ ለማዋቀር “እስኪፕ ዚስ ኤንድ ዩዝ ማይ ኤዚስቲንግ ኢሜል” የሚለውን ጠቅ ያድርጉ። በመቀጠልም ስምዎን፣ የኢሜል አድራሻዎን እና ለኢሜልዎ የማለፊያ ቃል ያስገቡ።

እንደ ጂሜል ያለ ስመጥር ነጻ የኢሜል አገልግሎት የሚጠቀሙ ከኾነ ‘ኮንቲኒው’ የሚለውን ጠቅ ሲያደርጉ ተንደርበርድ የኢሚልዎን ቅንብር በቀጥታ ማግኘት አለበት። ይህን ማድረግ ካልቻለ የIMAP እና የSMTP ቅንብሩን በእጅ ማቀናበር ይኖርብዎታል። የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢዎን ወይም የኢሜል ቅንብርን ማዋቀር የሚችል ሙያዊ እውቀት ያለው ጓደኛዎን እርዳታ ይጠይቁ። አንዳንዴ ተንደርበርድ ትክክለኛውን ቅንብር ሊግምት ይችላል።

ባለ ሁለት ማጥሪያ ማመሳከሪያ ከጎግል (የስጋት ሞዴልዎን መሠረት አድርገው ሊጠቀሙ ይገባል) ጋር የሚጠቀሙ ከኾነ መደበኛ የጂሜል ማለፊያ ቃልዎን ከተንደርበርድ ጋር መጠቀም አይችሉም። ይልቁንም የጂሜል አድራሻዎን በተንደርበርድ ለመጠቀም ለመተግበሪያው የተወሰነ አዲስ የማለፊያ ቃል መፍጠር ያስፈልግዎታል። ይህን ለማድረግ የራሱ የጎግል መመሪያን ይመልከቱ። 

ተንደርበርድን ማዋቀር ከጨረሱ በኋላ ኢሜልዎን ለመመልከት ደን የሚለውን ጠቅ ያድርጉ። ከዚያም ኢሜልዎትን ለመጫን ከላይ በግራ በኩል ያለው “ኢንቦክስ” የሚለው ላይ ጠቅ ያድርጉ።

አሁን ተንደርበርድን ጭነው ከኢሜልዎ ጋር እንዲሰራ አዋቅረዋል። በመቀጠል ለተንደርበርድ የGPG ቅጥያ የሆነውን ኤኒግሜልን መጫን ይኖርብዎታል። በተንደርበርድ የላይኛው ቀኝ ክፍል የሚገኘውን ምናሌ አዶ ጠቅ ያድርጉ እና አድ-ኦንስ የሚለውን ይምረጡ።

በላይኛው ቀኝ ክፍል በሚገኘው የመፈለጊያ ሳጥን “ኤኒግሜል”ን ይፈልጉ።

ኤኒግሜልን አውርዶ ለመጫን ከኤኒግሜል ቅጥያ አጠገብ ያለውን ኢንስቶል የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ። ሲያበቃ ተንደርበርደን እንደገና ለማስጀመር ‘ሪስታርት ናው’ የሚለውን ጠቅ ያድርጉ።

ለመጀመሪያ ጊዜ ኤኒግሜልን አስችለው ተንደርበርድን ሲከፍቱት የOpenPGP ማዋቀሪያ አዋቂን ይከፍታል። ‘ካንስል’ የሚለውን ጠቅ ያድርጉ። ይልቁን ኤኒግሜልን በእጅ (በትዕዛዝ) እናዋቅረዋለን።

ሜኑ አዝራር ላይ ጠቅ ያድርጉ፤ በፕሪፈረንስ ላይ ያንዣብቡ እና አካውንት ሴቲንግ የሚለውን ይምረጡ።

ወደ OpenPGP ሰኪዩሪቲ ትር ይሂዱ። “ኢንኤብልOpenPGP ሰፖርት (ኤኒግሜል) ፎር ዚስ አይደንቲቲ” የሚለው መመልከቱን ያረገግጡ። “ዩዝ ስፔስፊክ OpenPGP ኪይ አይዲ” የሚለው ይምረጡ እና ቁልፍዎ ካልተመረጠ ሴሌክት ኪይ የሚለውን ጠቅ በማድረግ ቁልፍዎን ይምረጡ።

በተጨማሪም “ሳይን ነን-ኢንክሪፕትድ ሜሴጅ ባይ ዲፎልት”፣ “ሳይን ኢንክሪፕትድ ሜሴጅ ባይ ዲፎልት”፣ እና “ዩዝ PGP/MIME ባይ ዲፎልት” የሚሉትን ሲያመለክቱ ነገር ግን “ኢንክሪፕት ሜሴጅ ባይ ዲፎልት” የሚለው ማመልከት የለብዎትም።

ኢሜል የሚልኩላቸውን ብዙዎቹ ሰዎች PGPን የሚጠቀሙ ከሆነ (ወይም እንዲጠቀሙ ማበረታታት የሚፈልጉ ከሆነ) በነባሪ መልክትዎ የተመሰጠረ እንዲሆን ይፈልጉ ይሆናል። ሁሉንም የሚልኳቸውን ኢሜልዎች ማመስጠር አይነተኛ ቢሆንም ነገር ግን ሁሌም ይህን ማድረግ አይቻልም። ያስታውሱ የተመሰጠረ ኢሜል መላክ የሚችሉት የPGP ተጠቃሚ ለሆኑ እና በኪይቼንዎ ውስጥ የአደባባይ ቁልፋቸው ላለዎት ሰዎች ብቻ ነው። ስለዚህ ለአብዛኛው ሰው እያንዳንዱን ኢሜል በእጅ እንዲመሰጠር መምረጥ የተሻለ ይሰራል።

ቀጥሎ ሁሉንም ቅንብሮች እንዲያስቀምጥ ኦኬ የሚለውን ጠቅ ያድርጉ።

እንኳን ደስ አለዎት! አሁን ተንደርበርድ እና ኤኒግሜልን አቀናብረዋል! ጥቂት ምክሮች፦

  • የሜኑ አዝራር ላይ ጠቅ አድርገው OpenPGP ላይ ያንዣብቡ እና የኤኒግሜል አብሮገነብ የፒጂፒ ቁልፍ አስተዳዳሪን ለማየት ‘ኪይ ማኔጅመንት’ የሚለውን ይክፈቱ። ይህም ከGPG ኪይቼን አክሰስ ጋር ተመሳሳይ ሲኾን የሚፈልጉትን መጠቀም የእርስዎ ምርጫ ነው።
  • አዲስ መልዕክትን ሲያቀናብሩ በመስኮቱ ታችኛው የቀኝ ክፍል ሁለት አዶዎች አሉ። እነዚህም ዲጂታል ፊርማ የሚፈርሙበት የእስክሪብቶ እና ኢሜሉን የሚያመሰጥሩበት የቁልፍ ምልክት ናቸው። እነኚህ አዶዎች ወርቃማ ከኾኑ ተመርጠዋል ማለት ሲኾን ብርማ ከኾኑ ግን አልተመረጡም ማለት ነው። እየከተቡ ያሉትን ኢሜል ለመፈረም እና ለማመስጠር ላያቸው ላይ ጠቅ በመድረግ ይቀሯቸው።

JavaScript license information