የሰርጎ ገብ ጥቃት (MITM)
የተመሰጠረ ፈጣን የመልዕክት አገልግሎትን ተጠቅመው ከጓደኛዎ ተኽላይ ጋር እያወሩ ነው እንበል። እየተነጋገሩ ያሉት በትክክል ከሱ ጋር እንደኾነ ለማጣራት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት የት ከተማ ላይ እንደኾነ እንዲነግርዎት ይጠይቁታል። ‘ጅማ’ ብሎ ይመልስልዎታል። ይህም ትክክል ነው። እንደ አለመታደል ኾኖ ሁለታችሁ ሳታስተውሉት ሌላ ግለሰብ የመስመር ላይ ግንኙነታችሁን ጠልፎ ይሰማል። ለመጀመሪያ ጊዜ ከተኽላይ ጋር በመስመር ላይ ሲገናኙ በትክክል ከተኽላይ ጋር ሳይኾን ከዚህ ማንንቱ ከማይታወቅ ግለሰብ ጋር ኾኖ እሱ ደግሞ ከጓደኛዎት ተኽላይ ጋር ያገናኞታል። እርስዎ ጥያቄውን ያቀረብኩት ለተኽላይ ነው ብልው ሲያስቡ ጥያቄውን በእርግጥ የጠቁት ግን በመሃከል ለገባው ግለሰብ ነው። ግለሰቡም ጥያቄዎትን ተቀብሎ ለጓደኛዎ ለተኽላይ ያስተላልፋል። መልሱንም ተቀብሎ ለእርስዎ ይሰጣል። ምንም እንኳ ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ ከተኽላይ ጋር እንደሚገናኙ ቢያስቡም፤ እየተገናኙ ያሉት ግን ከሰላዩ ጋር ነው። በተመሳሳይ ተኽላይም እንዲሁ ያስባል። ይህ የሰርጎ ገብ ጥቃት ይባላል። በመሃል ሰርጎ በመግባት ስለላ የሚያካሂድ አጥቂ የእርስዎን ግንኙነቶች እንደ ፈለገ ከመሰለሉም ባሻገር በግንኙነትዎ መካከልም አሳሳች መልዕክቶችን ሊያስገባ ይችላል። ደህንነት ተኮር የኢንትርኔት ግንኙነት ሶፍትዌሮች ሁሉንም ዓይነት የኢንተርኔት ግንኙነቶች የመሰለል አቅም ካላቸው ከሰርጎ ገብ ጥቃቶች መከላከል አለባቸው።