ለዊንዶውስ የOTR አጠቃቀም

OTR (ኦፍ-ዘ-ሪከርድ) የሚባለው የፈጣን መልዕክት ወይም የመስመር ላይ ውይይት መሣሪያ ተጠቃሚዎች ሚስጥራዊነቱን የተጠበቀ ውይይት እንዲያደርጉ የሚያስችል ስርዓት ነው። በዚህ መመሪያ በዊንዶውስ ኮምፒውተር ነጻ እና ነጻ-ምንጨ ኮድ የፈጣን መልዕክት ደምበኛ በኾነው በፒጅን አማካኝነት OTRን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ይማራሉ።

  Anchor link

OTR ከምዝገባ ውጪ (ኦፍ ዘ ሪከርድ) ማለት መልዕክት ማስተላለፊያ መንገዶችን በመጠቀም ምስጢራዊ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዲያደርጉ የሚያስችል ስርዓት ነው። OTR ይህን ደህንነት የሚያጎኛፅፈው፦

  • በጽሑፍ አማካኝነት የሚደረጉ ውይይቶችን በማመስጠር
  • የሚወያዩትን ሰው ትክክለኛ ማንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ብልሃት በማጣመር
  • አገልጋዩ (ሰርቨር) እንዲገባ ባለመፍቀድ። አገልጋዩ ከገባ ግን ውይይቶችን ያገኛል፤ ምስጢራዊነቱም ያበቃል ማለት ነው

ይህ ከጎግል “ከምዝገባ ውጪ” ከሚደረግ ውይይት ጋር መምታታት የለበትም። የጎግል ‘ከምዝገባ ውጪ’ የሚያደርገው የመወያያ መተግበሪያዎን አለማስቻል ሲኾን ውይይቱን የማመስጠር ወይም የውይይቱን ተሳታፊዎች የማመሳከር አቅም የለውም። በማይክሮሶፍት ዊንዶውስ ላይ በርካታ የOTR አጠቃቀም መንገዶች ቢኖሩም የፒጂን መወያያ ደምበኛ ከፒጂን-OTR ተሰኪ ጋር መጠቀም እጅግ በጣም አስተማማኝ እና ለአጠቃቀምም ቀላል መሳሪያ ኾኖ ተገኝቷል።

የዊንዶውስ ኮምፒውተሮች ፈጣን መልዕክት መላኪያ የሚጠቀሙ ደንበኛ ከኾኑ፤ ፒጂን በነባሪ ውይይት ውስጥ በቀጥታ ይገባል። ነገር ግን ይህንን ገጽታ ያለማስቻል (ያለመተግበር) አቅም አለዎት። ይህ ከተባለ ዘንዳ በሌላ ጥግ ውይይት የሚያደርገውን ግለሰብ መቆጣጠር እንደማይችሉ ይወቁ። ምንም እንኳ እርሶ መግባትን ባያስችሉም በሌላ ወገን ያለው ግለሰብ ሊገባ ወይም የንግግሮን ስክሪን ቅጂ ሊወስድ ይችላል።

ፒጂንን እና OTRን በአንድ ላይ መጠቀም ያለብኝ ለምንድን ነው? Anchor link

የጎግል ሃንግአውት ወይም የፌስቡክ ድረ ገጽን በመጠቀም የጎግል ሃንግአውት ወይም የፌስቡክ የጽሑፍ ውይይት በሚያደርጉበት ወቅት ውይይትዎ በHTTPS የተመሰጠረ ነው። ይህ ማለት የውይይትዎ ይዘት በዝውውር ላይ እያለ ከሰርጎ ገቦች እና ከሌላ ሦስተኛ ወገን የተጠበቀ ነው ማለት ነው። ነገር ግን የውይይትዎ ቁልፍ ካላቸው ከጎግል ወይም ከፌስቡክ እይታ የተጠበቀ ነው ማለት አይደለም። ይህንንም ለመንግሥት አሳልፈው ሊሰጡ ይችላሉ።

ፒጅንን በኮምፒውተርዎ ላይ ከጫኑ በኋላ በተመሳሳይ ሰዓት የተለያዩ መለያዎችን በመጠቀም መግባት ይችላሉ። ለምሳሌ ጎግል ሃንግአውትን፣ ፌስቡክን እና XMPPን በተመሳሳይ ጊዜ መጠቀም ይችላሉ። በተጨማሪም ፒጂን OTRን ሳይጠቀሙ እነኚህን መሣሪያዎች በመጠቀም እንዲወያዩ ይፈቅዳል። OTR የሚሠራው በሁለቱም ወገን ያሉ ስዎች ሲጠቀሙት ብቻ ነው። ይህ ማለት በሌላ ወገን ያለው ግለሰብ OTRን በኮምፒውተሩ ላይ ካልጫነ፤ ፒጂንን በመጠቀም ውይይት ማድረግ ይችላሉ።

በተጨማሪም ፒጂን የሚያወሩት ግለሰብ በርግጠም ተፈላጊው ሰው ነው ብለው የሚገምቱት እንደኾነ እና ለMITM ጥቃት ያልተጋለጡ መኾንዎን የሚገልጽ ከመስመር ውጪ የኾነ ማረጋገጫን እንዲያደርጉ ይፈቅዳል። ለእያንዳንዱ ውይይት ለእርሶ እና እየተወያዩት ላለው ሰው ያለውን የቁልፍ የጣት አሻራ ማየት የሚያስችል ምርጫ ይሰጥዎታል። “ቁልፍ የጣት አሻራ” ማለት የተለያዩ ምልክቶች ለምሳሌ እንደዚህ ያለ “342e 2309 bd20 0912 ff10 6c63 2192 1928,” ሲኾን ይህም ረዘም ያለ የደባባይ ቁልፍን ለማረጋገጥ የሚጠቅም ነው። ከማን ጋር እንደሚወያዩ ለማወቅ እና በውይይትዎ ውስጥ ጣልቃ ገቦች እንደሌሉ ለማጣራት የጣት አሻራዎን ሌላ የመገናኛ ዘዴ በመጠቀም ማለትም በትዊተር የቀጥታ መልዕክት ወይም በኢሜል ይቀያየሩ።

ውስንነቶች ፦ ፒጂን እና OTRን መጠቀም የሌለብኝ መቼ ነው? Anchor link

ቴክኖሎጂስቶች አንድ ፕሮግራም ወይም ቴክኖሎጂ ለውጭ ጥቃት ተጋላጭነቱን ለመግለጽ የሚጠቀሙበት ቃል አለ። ይህም ቃል ትልቅ “የጥቃት ገጽታ” አለው የሚል ነው። ፒጂንም ትልቅ የጥቃት ገጽታ አለው። በጣም የተወሳሰበ ፕሮግራም ያለው ሲኾን ደህንነትን ቅድሚያ ባላደረገ መርህ የተጻፈ ነው። በርግጠኝነት የተለያዩ ስህተቶች ያሉበት ሲኾን ከእነኚህም ጥቂቶቹ ስህተቶች መንግሥታት ወይም ትላልቅ ኩባንያዎች ፒጅንን የሚጠቀሙ ኮምፒውተሮችን ሰብሮ ለመግባት ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ውይይትዎን ለመደበቅ እና ሁሉንም ሰው ከሚያጠቃ ያልተነጣጠረ የኢንተርኔት መስመር ላይ ስለላ ራስን ለመከላከል ፒጂንን መጠቀም ታላቅ የመከላከያ ዘዴ ነው። ነገር ግን በግል አቅም ካለው አካል ለምሳሌ የመንግሥታት የጥቃት ዒላማ እንደሚኾኑ ከተሰማዎት ጠበቅ ያለ ጥንቃቄ መውሰድ ለምሳሌ በPGP የተመሰጠረ የኢሜል ስርዓት መጠቀም ይኖርብዎታል።

ፒጅንን ማግኘት Anchor link

በዊንዶውስ ላይ ፒጅንን ለመጫን ከፒጅን የማውረጃ ገጽ ላይ የሚጭነውን ማውረድ ይቻላሉ።

ሃምራዊ ቀለም ያለውን ዳውንሎድ የሚለውን ትር ጠቅ ያድርጉ። የተለየ የመጫኛ ሰነድ ስለሚመርጡ አረንጓዴውን 'ዳውንሎድ ናው' የሚለው አዝራር ላይ ጠቅ እንዳያደርጉ። ይህም ወደ ማውረጃ ገጽ ይውስድዎታል።

የተለየ የመጫኛ ሰነድ ስለሚመርጡ አረንጓዴውን ዳውንሎድ ናው የሚለው አዝራር ላይ ጠቅ እንዳያደርጉ። ሁሉንም መረጃ ያላያዘ እና የፒጂን ነባሪ መጫኛ አነስተኛ በመኾኑም ፋይሉን ያወርድልዎታል። ይህም አንዳንድ ጊዜ ላይሳካ ይችላል። ስለዚህም ሁሉንም የመጫኛ አስፈላጊ ግብዓቶች የያዘውን “ኦፍላየን ኢንስቶለር”ን መጠቀም የተሻለ ተሞክሮ ሊሰጥዎት ይችላል። “ኦፍላየን ኢንስቶለር” የሚለው አያያዥ ላይ ጠቅ ያድርጉ። ከዚያም “ሶርስፎርጅ” ወደሚል ሌላ አዲስ ገጽ ይውስድዎት እና ከጥቂት ሰከንዶች በኋላ አነስተኛ ብቅ ባይ ሰነዱን ማስቀመጥ እንደሚፈልጉ እና እንደማይፈልጉ ይጠይቅዎታል።

ያስተውሉ! ፒጅንን የማውረጃ ገጽ “HTTPS”ን ስለሚጠቀም በአንጻሩ በድብቅ በኮምፒውተርዎ ላይ ተፅዕኖ ለማድረስ ከሚሞክር አካል የተጠበቁ ነዎት። ነገር ግን የዊንዶውስ ስሪት የኾነውን የፒጂን ሶፍትዌርን ለማውረድ የሚመራዎ ድረ ገጽ በአሁኑ ጊዜ ሶርስፎርጅ ነው። ይህ ደግሞ ድብቅ ያልኾነውን “HTTP”ን የሚጠቀም በመኾኑ ምንም ዓይነት ከለላን አይሰጥም። ይህ ማለት ያወረዱት ሶፍትዌር በኮምፒውተርዎ ላይ ከማውረድዎ በፊት ተጽዕኖ ውስጥ የገባ ሊኾን ይችላል።

ይህ ተጋላጭነት በብዛት የሚመጣው አቅራቢያዎ ያለውን የኢንተርኔት መሠረተ ልማት የመጠቀም አቅም ያለው ግለሰብ እርሶ ላይ ያነጣጠረ የመስመር ላይ ስለላ ማካሄድ ሲሞክር (ለምሳሌ ሸረኛ የኾነ የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢ) ወይም መንግሥት ኾን ብሎ ዜጎቹን ለመሰለል ከሚያሰራጨው ደህንነቱ ያልተጠበቀ ሶፍትዌር ሊኾን ይችላል። የ HTTPS በሁሉም ቦታ ቅጥያ የሶርስፎርጅ ማውረጃ URLን እንደ አዲስ ወደ HTTPS ቀይሮ ሊጽፈው ይችላል። በመኾኑም ማንኛውንም ሶፍትዌር ከማውረድዎ በፊት HTTPS በሁሉም ቦታ በቅድሚያ እንዲጭኑ ይመከራሉ። በተጨማሪም በእኛ ልምድ ሶርስፎርጅ አብዛኛውን ጊዜ ግራ የሚያጋባ አንድ ሙሉ ገጽ ማስታወቂያዎች በማውረጃ ገጹ ላይ አግኝተናል። ይህም ሰዎች የማይፈልጉትን ነገር እንዲጭኑ ሊያታልላቸው ይችላል።.  እነዚህ ግራ የሚያጋቡ ማስታወቂያዎችን ለመከላከል ከማንኛውም ሶፍትዌር በፊት ማስታወቂያ የሚዘጋ ሶፍትዌር መጫን ይችላሉ። ያስታውሱ ደህንነቱ ካልተጠበቀ ድረ ገጽ ፋይሎችን ከማውረዶ በፊት የስጋት ሞዴልዎን ማስላት ይጠበቅብዎታል።

አብዛኛቹ የድር ማሰሻዎች ይህንን ሰነድ ማውረድ እንደሚፈልጉ ማረጋገጫ ይጠይቅዎታል። የኢንተርኔት ኤክስፕሎረር 11ኛው ብጅት በድር መዳሰሻው ገጽ የታችኛው ክፍል ላይ ብርቱካናማ ክፈፍ ያለው አሞሌ ያሳያል።

ለማንኛውም የድር ማሰሻ እጅግ በጣም ተመራጭ የሚኾነው ወደሚቀጥለው እንቅስቃሴ ከመግባትዎ በፊት ያወረዱትን ሰነድ ማስቀመጥዎ ነው። ይህንን ለማድረግም “ሴቭ” የሚለው አዝራር ላይ ጠቅ ያድርጉ። በነባሪ አብዛኞቹ የድር ማሰሻዎች የወረደውን ሰነድ በማውረጃ ማህደር ውስጥ ያስቀምጣሉ።

OTRን ማግኘት Anchor link

ፒጂን-OTR የተባለውን ለፒጂን የሚኾን የOTR ተሰኪ መጫኛን ከዚህ የOTR ማውረጃ ገጽ ላይ ማውረድ ይችላሉ።

“ዳውንሎድ” የሚለውን ትር ጠቅ በማድረግ ወደ “ዳውንሎድስ” የገጽ ክፍል ይሂዱ። ከዛ “ዊን32 ኢንስቶለር ፎር ፒጅን” የሚለውን አገናኝ ጠቅ ያድርጉ።

አብዛኞቹ የድር ማሰሻዎች ይህንን ሰነድ ማውረድ እንደሚፈልጉ ማረጋገጫ ይጠይቅዎታል። የኢንተርኔት ኤክስፕሎረር 11ኛው ስሪት በድር መዳሰሻው ገጽ የታችኛው ክፍል ላይ ብርቱካናማ ክፈፍ ያለው አሞሌ ያሳያል።

ለማንኛውም የድረ ገጽ ማሰሻ እጅግ በጣም ተመራጭ የሚኾነው ያወረዱትን ሰነድ ወደሚቀጥለው እንቅስቃሴ ከመግባትዎ በፊት ማስቀመጥ ነው። ስለዚህ “ሴቭ” የሚለው አዝራር ላይ ጠቅ ያድርጉ። በነባሪ አብዛኞቹ የድር ማሰሻዎች የወረደውን ሰነድ በማውረጃ ማኅደር ውስጥ ያስቀምጣሉ።

ፒጅንን እና ፒጅን-OTR ካወረዱ በኋላ በማውረጃ ማኅደርዎ ውስጥ ሁለት አዳዲስ ሰነዶች ሊኖርዎት ይገባል፦

ፒጅንን መጫን Anchor link

የዊንዶውስ ኤክስፕሎረር መስኮትን ክፍት ያድርጉ እና pidgin-2.10.9-offline.exe የሚለው ፋይል ላይ ሁለቴ ጠቅ ያድርጉ። በመቀጠልም ይህ ፕሮግራም እንዲጫን እንደሚፈቅዱ ይጠየቃሉ። ከዚያም “የስ” የሚለውን አዝራራ ጠቅ ያድርጉ።

ትንሽ መስኮት ይከፈትና ቋንቋ እንዲመርጡ ይጠይቅዎታል። ከዛ “ኦኬ” የሚለው አዝራር ላይ ጠቅ ያድርጉ።

አጠር ያለ አጠቃላይ የአጫጫን ሂደቱን የሚያብራራ መስኮት ይከፈታል። “ኔክስት” የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ።

አሁን የፈቃድ አጠቃላይ ክለሳ ክፍሉን ያገኛሉ። “ኔክስት” የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ።

አሁን ምን ዓይነት የተለያዩ ምንዝሮች እንደተጫኑ ማየት ይችላሉ። ቅንብሮቹን እንዳይቀይሯቸው። “ኔክስት” የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ።

አሁን ፒጂን በኮምፒውተርዎ ውስጥ የት እንደሚጫን ማየት ይችላሉ። እነዚህን መረጃዎች እንዳይቀይሯቸው። “ኔክስት” የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ።

አሁን “ኢንስታሌሽን ኮምፕሊት” እስከሚል ድረስ ወደታች እየተንሸራተተ በራሱ የሚወርድ ጽሑፍ ይመለከታሉ። “ኔክስት” የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ።

በመጨረሻም የፒጂን መጫኛ የመጨረሻውን መስኮት ያገኛሉ። “ፊኒሽ” የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ።

ፒጅን-otrን መጫን Anchor link

ወደ ዊንዶውስ ኤክስፕሎረር መስኮት በመመለስ እና በመክፍት pidgin-otr-4.0.0-1.exe የሚለውን ሁለቴ ጠቅ ያድርጉ። በመቀጠልም ይህንን ፕሮግራም እንዲጫን እንደሚፈቅዱ ይጠየቃሉ። “የስ” የሚለውን አዝራራ ጠቅ ያድርጉ።

አጠር ያለ አጠቃላይ የአጫጫን ሂደቱን የሚያብራራ መስኮት ይከፈታል። በመቀጠል “ኔክስት” የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ።

አሁን የፈቃድ አጠቃላይ ክለሳ ክፍሉን ያገኛሉ። “አይ አግሪ” የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ።

ፒጂን-otr በኮምፒውተርዎ ውስጥ የት እንደሚጫን ማየት ይችላሉ። እነዚህን መረጃዎች እንዳይቀይሯቸው። “ኢንስቶል” የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ።

በመጨረሻም የፒጂን-otr መጫኛ የመጨረሻውን መስኮት ይመለከታሉ። ከዛ “ፊኒሽ” የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ።

ፒጂንን ማዋቀር Anchor link

ስታርት የሚለው ምናሌ ላይ ይሂዱና የዊንዶውስ ምልክት ላይ ጠቅ ያድርጉ። ፒጂንን ከምናሌው ላይ ይምረጡ።

መለያ ወይም አካውንት ማከል Anchor link

ፒጅን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲንደረደር ይህንን መለያ ወይም አካውንት መጨመር የሚያስችል የእንኳን ደህና መጣችሁ መስኮት ያሳይዎታል። እስካሁን ምንም ዓይነት የተዋቀረ መለያ (አካውንት) ስለሌልዎት “አድ” የሚለው አዝራር ላይ ጠቅ ያድርጉ።

አሁን “የአድ አካውንት” መስኮትን ያያሉ። ፒጂን ከተለያዩ የመወያያ ስርዓቶች ጋር መስራት ቢችልም እኛ ግን XMPP ወይም በቀድሞ ስሙ ጃብር ላይ እናተኩራለን።

የፕሮቶኮል ማስገቢያ ላይ “XMPP” የሚለውን አማራጭ ይምረጡ።

የተጠቃሚ ስም ማስገቢያ ላይ የእርስዎን የXMPP ተጠቃሚ ስም ያስገቡ።

የጎራ ማስገቢያ ላይ የእርስዎን የXMPP መለያ ጎራ ያስገቡ።

የይለፍ ቃል ማስገቢያ ላይ የእርስዎን የXMPP የይለፍ ቃል ያስገቡ።

“ሪሜምበር ፓስወርድ” ማስገቢያ ላይ ያለውን ሳጥን መምረጥዎ መለያዎን በቀላሉ መጠቀም እንዲችሉ ይረዳዎታል። እዚህ ጋር ማስታወስ የሚገባዎት ነገር “ሪሜምበር ፓስወርድ” የሚለውን ከመረጡ የማለፊያ ቃልዎት በኮምፒውተርዎ ላይ ይቀመጣል። ይህም ማለት ማንኛውም ኮምፒውተርዎን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚጠቀም ሰው የማለፊያ ቃልዎን በቀላሉ ሊያገኝ ይችላል። ይህ የሚያሳስብዎት ጉዳይ ከሆነ ይህን ሳጥን በፍጹም አይምረጡ። ከዛም ፒጅንን በከፈቱ ቁጥር የXMPP መለያ የይለፍ ቃልዎን በየጊዜው እንዲያስገቡ ይጠየቃሉ።

ተጓዳኝ ማከል/መጨመር Anchor link

አሁን የመስመር ላይ ውይይት ለማድረግ አንድ ሰው መጨመር ይፈልጋሉ። “በዲስ” የሚለው ምናሌ ላይ ጠቅ ያድርጉ እና “አድ በዲ” የሚለውን ይምረጡ። ከዛም “አድ በዲ” የሚል መስኮት ይከፈታል።

በ“አድ በዲ” መስኮት ውስጥ ውይይት ለማድረግ የሚፈልጉትን ግለሰብ የተጠቃሚ ስም ማስገባት ይችላሉ። ይህ ግለሰብ የሚጠቀመው አገልጋይ ከእርሶ ጋር ተመሳሳይ መሆን አይጠበቅበትም። ነገር ግን ተመሳሳይ የሆነ ስርዓት ልክ እንደ XMPP መጠቀም አለበት።

በ“በዲስ ዩዘርኔም” ማስገቢያ ላይ የጓደኛዎን የተጠቃሚ ስም ከጎራው ስም ጋር ያስገቡ። ይህም የኢሜል አድራሻን ይመስላል።

“ኤሊየስ (ኦፕሽናል)” የሚለው ማስገቢያ ላይ ለጓደኛዎ የመረጡትን ቅጽል ስም ማስገባት ይችላሉ። ይህ ሙሉ በሙሉ በምርጫ የሚደረግ ቢኾንም የግለሰቡ የXMPP መለያ ለማስታውስ የሚያስቸግር በሚሆንበት ወቅት ሊጠቅምዎ ይችላል።

“አድ” የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ

አንዴ “አድ” የሚለው አዝራር ላይ ጠቅ ካደረጉ በኋላ፤ አበበ እርስዎ እንዲያክሉት/እንዲጨምሩት ፈቃድ እንደሚሰጥ የሚጠይቅ መልዕክት ያገኛል። አበበ መልዕክቱን ካገኘ በኋላ የእርስዎን መለያን ሲጨምር ለእርስዎም ተመሳሳይ ጥያቄ ይመጣልዎታል። “አውቶራይዝ” የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ።

የOTR ተሰኪን ማዋቀር Anchor link

አሁን ደህንነቱ የተጠበቀ የመስመር ላይ ውይይት ለማድረግ የOTR ተሰኪን ያዋቅራሉ። “ቱልስ” ምናሌ ላይ ጠቅ ያድርጉ እና “ፕለጊንስ” የሚለውን ምርጫ ይምረጡ።

“ኦፍ-ዘ-ሪከርድ ሜሴጂንግ” የሚለውን ምርጫ ወደታች ያሸብልሉ እና ሳጥኑን ይምረጡ። “ኦፍ-ዘ-ሪከርድ ሜሴጂንግ” ማስገቢያ ላይ ጠቅ ያድርጉ፤ በመቀጠልም “ኮንፊገር ፕለጊን” የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ።

አሁን “ኦፍ-ዘ-ሪከርድ ሜሴጂንግ” ማቀናበሪያ መስኮት ያያሉ። እዚህ ጋር “ኖ ኪይ ፕረዘንት” እንደሚል ያስተውሉ። “ጀነሬት” የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ።

አሁን ትንሽ መስኮት ይከፈት እና ቁልፍ ያመነጫል። ሲጨርስ “ኦኬ” የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ።

አዲስ መረጃ ይመለከታሉ፦ ባለ 40 የጽሑፍ ሕብረ-ቁምፊ፤ እያንዳንዳቸው ስምንት ቁምፊ ያላቸው አምስት ቡድኖች ያገኛሉ። ይህ የእርስዎ የOTR የጣት አሻራ ነው። “ክሎዝ” የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ።

አሁን በ’ፕለጊን’ መስኮት የሚገኘውን “ክሎዝ” የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ።

ደህንነቱ የተጠበቀ የመስመር ላይ ውይይት ማድረግ Anchor link

አሁን ከአበበ ጋር ደህንነቱ የተጠበቀ ውይይት ማካሄድ ይችላሉ። ሁለታችሁም መልዕክት መላላክ ትችላላችሁ። ነገር ግን ደህንነቱ የተጠበቀ ውይይት እስካሁን ማድረግ አትችሉም። ምንም እንኳን የXMPP አገልጋይን ተጠቅመው ቢወያዩም በእርስዎና በአበበ መካከል ያለው ግንኙነት ከስለላ የተጠበቀ አይደለም። የውይይት መስኮትዎ የቀኝ የታችኛው ክፍልን ቢመለከቱ በቀይ የተጻፈ “ኖት ፕራይቬት” የሚል ማሳሰቢያ ያገኛሉ። “ኖት ፕራይቬት” የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ።

አዲስ ምናሌ ይከፍታል ከዛ “አውተንትኬት በዲ” የሚለውን ይምረጡ።

መስኮት ይከፈት እና “ሃው ውድ ዮ ላይክ ቱ አውተንቲኬት ዩር በዲ?” የሚል ጥያቄ ይጠይቅዎታል።

ተቆልቋዩ ሶስት ምርጫ አለው፦

የጋራ ሚስጥር Anchor link

የጋራ ሚስጥር እርስዎ እና በሌላ ጥግ ያለው ሊወያዩት የሚፈልጉት ግለሰብ ለመጠቀም የተስማማችሁበት አጭር ጽሁፍ ነው። ይህንን በአካል ተገኝቶ እንጂ እንደ ኢሜል ወይም ስካይፒ ባሉ ደህንነታቸው ባልተጠበቀ የመገናኛ መንገግዶች መለዋወጥ በፍጹም የለባችሁም።

ይህንን አጭር ጽሑፍ እርስዎ እና ጓደኛዎ በጋራ ማስገባት ይኖርባችኋል። በመቀጠል “አውተንቲኬት” የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ።

የጋራ ሚስጢርን ማረጋገጫ ጠቃሚ የሚኾነው እርሶ እና ጓደኛዎ ቀደም ብለው ለመወያየት እቅድ የያዛችሁ ከኾነ እና በምትጠቀሙባቸው ኮምፒውተሮች ላይ የOTR የጣት አሻራ ያልፈጠራችሁ እንደኾነ ነው።

በትዕዛዝ የጣት አሻራ ማረጋገጫ Anchor link

በትዕዛዝ የጣት አሻራ ማረጋገጫ ጠቃሚ የሚኾነው ጓደኛዎት የጣት አሻራውን ከሰጠዎት እና አሁን በፒጂን የሚገናኙ ከኾነ ነው። ጓደኛዎ ኮምፒውተር የሚቀይር ወይም አዲስ የጣት አሻራ የሚፈጥር ከኾነ ይህ ጥቅም አይኖረውም።

የተሰጠዎት የጣት አሻራ እና በስክሪኑ ላይ የሚመለከቱት የጣት አሻራ የሚመሳሰል ከኾነ “አይ ሀቭ” የሚለውን ይምረጡ እና “አውተንትኬት” የሚለው አዝራርን ጠቅ ያድርጉ።.

ጥያቄ እና መልስ Anchor link

የጥያቄ እና መልስ ማረጋገጫ ጠቃሚ የሚኾነው ጓደኛዎን የሚያውቁ ነገር ግን የጋራ ሚስጥርም ኾነ የጣት አሻራ ያልተጋራችሁ ከኾነ ነው። ይህ ዘዴ ጠቃሚ የሚኾነው ማረጋገጫው ሁለታችሁም በምታውቁት ነገር ለምሳሌ የጋራ ትውስታ ወይም ክስተት ላይ የተመሰረተ እንደኾነ ነው።

ሊጠይቁ የሚፈልጉትን ጥያቄ ያስገቡ። ሰዎች በጣም በቀላሉ እንዳይገምቱት እጅግ ቀላል ጥያቄ አያድርጉት። ሊመለስ የማይችል ከባድም አይሁን። የጥሩ ጥያቄ ምሳሌ ሊኾን የሚችለው “ድሬደዋ የሄድን እለት እራት የት ነው የበላነው?” ጥሩ ያልኾነ ጥያቄ ደግሞ “አሳይታ የበረዶ ሸርታቴ መጫወት ይቻላል?”

መልሶቹ በትክክል መመሳሰል አለባቸው። በመኾኑም ለጥያቄዎ መልስ ሲሰጡ ይህንን ማወቅ አለብዎት። መልሱ የሚጻፍበት ስርዓተ ጽሑፍ ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብዎታል። ስለዚህ መልሱ የሚጻፍበትን የስርዓተ ጽሑፍ መመሪያን በቅንፍ ውስጥ ማስቀመጥን ከግምት ውስጥ ያስገቡ።

ጥያቄ እና መልሱን ያስገቡ እና “አውተንትኬት” የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ።

ጓደኛዎ መልስ የሚገባውን ጥያቄ የሚያሳይ ምስኮት ይከፈታል። ጥያቄውን መልሶ “አውተንትኬት” የሚለውን አዝራር ጠቅ ማድረግ ይኖርበታል። በመቀጠል የማረጋገጡ ሂደት የተሳካ መሆኑን የሚገልጽ መልዕክት ይገኛል።

ጓደኛዎ የማረጋገጫ ቅደም ተከተሉን ከፈጸመ በኋላ የማረጋገጫ ሂደቱ እንደተሳካ የሚገልጽ መስኮት ያገኛሉ።

የሁለታችሁም ግንኙነት ደህንነቱ የተጠበቀ መኾኑን ለማረጋገጥ ጓደኛዎ የእርስዎን መለያ ማረጋገጥ ይኖርበታል። ለአበበ እና ለአወቀ የሚከተለውን ይመስላል። በመወያያ መስኮቱ የታችኛው ቀኝ ክፍል የሚገኘውን “ፕራይቬት” የሚለውን አዶ ያስተውሉ።

ከሌሎች ስፍትዌሮች ጋር መስራት Anchor link

እውነተኝነትን ለማረጋገጥ የምንጠቀማቸው ዘዴዎች ከተለያዩ የመወያያ ሶፍትዌሮች ማለትም ጂትሲ፣ ፒጂን፣ አዲየም እና ኮፔት መካከል መስራት አለበት። በXMPP እና OTR ለመወያየት ተመሳሳይ የመወያያ ሶፍትዌሮችን መጠቀም አይጠበቅብዎትም ነገር ግን አልፎ አልፎ በሶፍትዌሩ ስህተቶች ሊገኑ ይችላሉ። OS X የመወያያ ሶፍትዌር የሆነው አዲየም ጥያቄ እና መልስ ማረጋገጫ ሂደት ወቅት ስህተት አለው። ከሌሎች ጋር የጥያቄ እና መልስ ማረጋገጫን በሚጠቀሙበት ወቅት ችግር ካጋጠመዎት የሚጠቀሙት አዲየምን እንደኾነ ያጣሩ እና ሌላ የማረጋገጫ ዘዴን መጠቀም እንደሚችሉ ይመልከቱ።

Last reviewed: 
2015-02-10
ይህ ገጽ ከእንግሊዘኛው ቅጂ የተተረጎመ ነው፡፡ የእንግሊዘኛው ቅጂ ምን አልባት የበለጠ የዘመነ ይሆናል፡፡
JavaScript license information