Surveillance
Self-Defense

የኪፓስኤክስ አጠቃቀም

ኪይፓስኤክስ የማለፊያ ቃል ካዝና ነው። ይህም ለተለያዩ ድረ ገጾች እና አገልግሎቶች የሚጠቀሟቸውን የማለፊያ ቃልዎችዎን ለማስቀመጥ የሚጠቀሙበት ፕሮግራም ነው። የማለፊያ ቃል ካዝና ጥሩ መሣሪያ ነው። ለሚጠቀሟቸው አገልግሎትዎት በሙሉ የተለያዩ እና ለመገመት የሚያስቸግሩ የማለፊያ ቃሎችን መጠቀም ያስችላል። እነኚህን የማለፊያ ቃሎች ማስታወስ አይጠበቅብዎትም። በምትኩ ሁሉንም የማለፊያ ቃሎችዎን ያስቀመጡበትን ውሂብ ጎታ መፍታት የሚያስችለውን አንድ ዋና የማለፊያ ቃል ብቻ ማስታወስ ይጠበቅብዎታል። የማለፊያ ቃል ካዝና ምቹ እና ሁሉንም የማለፊያ ቃሎችዎን በአንድ ቦታ ማደራጀት የሚያስችል ነው።

የማለፊያ ቃል ካዝናን መጠቀም ለአጥቂዎች እና ለተቀናቃኝዎች አንድ የጥቃት በር እና ግልጽ ዒላማን መፍጠር መቻሉ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ነው። ብዙዎቹ ጥቅም ላይ የሚውሉ የማለፊያ ቃል ካዝናዎች የጥቃት ተጋላጭነት እንዳላቸው ጥናቶች ያሳያሉ። ስለዚህ ይህ ለእርሶ ትክክለኛ መሳሪያ መኾኑን እና አለመኾኑን በሚወስኑበት ወቅት ጥንቃቄ መውሰድ አለብዎት።

Last reviewed: 
2015-11-23
ይህ ገጽ ከእንግሊዘኛው ቅጂ የተተረጎመ ነው፡፡ የእንግሊዘኛው ቅጂ ምን አልባት የበለጠ የዘመነ ይሆናል፡፡
 

የኪፓስኤክስ አሰራር Anchor link

ኪፓስኤክስ የሚሰራው የማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታ ከተባለ ፋይል ጋር ነው። እነኚህ የማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታዎች እንደስማቸው ሁሉንም የማለፊያ ቃሎችን የሚያጠራቅሙ ናቸው። ውሂብ ጎታዎቹ በኮምፒውተርዎ ዋና ዲስክ ላይ በሚጠራቀሙበት ወቅት የተመሰጠሩ ይሆናሉ። ስለዚህ ኮምፒውተርዎ ቢሰረቅ ወይም ቢጠፋ ኮምፒውተርዎን ያገኘው ሰው የማለፊያ ቃሎችዎን ማንበብ አይችልም።

የማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታ በሶስት መንገዶች ሊመሰጥር ይችላል። ይህም ዋና የማለፊያ ቃል በመጠቀም፣ ቁልፍ ፋይል በመጠቀም ወይም ሁለቱንም በአንድነት በመጠቀም ሊሆን ይችላል። የእያንዳንዱን ጥቅም እና ጉዳት እንመልከት።

 

ዋና የማለፊያ ቃልን መጠቀም Anchor link

ዋና የማለፊያ ቃል የሚሰራው እንደ ቁልፍ ነው። የማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታን ለመክፈት ትክክለኛ የዋና ማለፊያ ቃል ያስፈልግዎታል። ከዛ ውጪ ማንም ሰው የማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታ ውስጥ ምን እንዳለ ማየት አይችልም። የማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታዎን ደህንነት ለመጠበቅ ዋና የማለፊያ ቃልን ሲጠቀሙ ከግምት ውስጥ ሊያስገቧቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ።

 • ይህ የማለፊያ ቃል ሁሉንም የማለፊያ ቃሎችን የሚፈታ ስለሆነ ጠንካራ ሊሆን ይገባል! ይህ ማለት በቀላሉ ሊገመት የማይችል እና ረጅም መሆን አለበት። የማለፊያ ቃሉ በረዘመ ቁጥር የተሻለ ይሆናል! በተጨሪም ረጅም በሆነ መጠን የተለያዩ ምልክቶችን፣ አብይ ፊደላትን ወይም ቁጥሮችን ለመጠቀም ብዙ መጨነቅ አይጠበቅብዎትም። ሁሉም ትንሽ ፊደላት በሆኑ እና በመካከላቸው ክፍተት ባላቸው ስድስት ቃላት ብቻ የተፈጠረ የማለፊያ ቃል በአብይ እና ትንሽ ፊደላት፣ ቁጥሮች እና ምልክቶች ከተሰራ ባለ 12-ምልክት የማለፊያ ቃል ይልቅ ለመሰበር አዳጋች ነው።
 • ይህን የማለፊያ ቃል ማስታወስ ይጠበቅቦታል! ይህ አንድ የማለፊያ ቃል ሁሉንም ሌሎች የማለፊያ ቃሎችዎን እንዲያገኙ የሚረዳዎ ስለሆነ በወረቀት ላይ ሳይጽፉ ማስታወስ እንደሚችሉ ማረጋገጥ ይኖርብዎታል። ይህም ልክ እንደ ዳይስዌር ያለ በዘፈቀደ የተፈጠሩ የቃላት ስብስብን እንዲጠቀሙ ሌላው ምክንያት ነው። ያልተለመዱ የምልክቶች እና የአብይ ፊደላት ስብስብን ለማስታወስ ከመጣር ይልቅ ለማስታወስ ቀላል የሆኑ የተለመዱ ቃሎችን መጠቀም ይችላሉ።
 

ቁልፍ ፋይልን መጠቀም Anchor link

በአማራጭነት የማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታን ለማመስጠር ቁልፍ ፋይልን መጠቀም ይችላሉ። ቁልፍ ፋይል ልክ የማለፊያ ቃልን እንደሚጠቀሙ በተመሳሳይ መንገድ ይሰራል። የማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታዎን ለመፍታት በሚፈልጉበት በማንኛውም ወቅት ቁልፍ ፋይሉን ለኪፓስኤክስ ማስገባት አለብዎት። የቁልፍ ፋይሉ መቀመጥ ያለበት በፍላሽ ድራይቭ ወይም በሌላ ተንቀሳቃሽ ማህደረ-መረጃ ሲሆን ይህንንም ከኮምፒውተርዎ ጋር ማገናኘት ያለብዎት የማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታዎን መክፈት ሲያስፈልግዎ ብቻ ነው። የዚህም ጥቅሙ የኮምፒውተርዎ ዋና ዲስክ (የማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታዎ) በሰው እጅ ላይ ቢወድቅ እንኳን በውጫዊ ማህደረ መረጃ ከተቀመጠው የቁልፍ ፋይል ውጪ የማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታዎን መፍታት አይችሉም። (በተጨማሪም ለባላንጣዎ ቁልፍ ፋይልን መገመት ማንኛውንም የማለፊያ ቃል ከመገመት የበለጠ በጣም ከባድ ነው።) የእዚህ መንገድ የጎንዮሽ ጉዳቱ የማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታዎን ለመጠቀም በፈለጉ ቁጥር ፋይሉን ያስቀመጡበት ውጫዊ ማህደረ መረጃ በአቅራቢያዎ ሊያገኙት የግድ መሆኑ ነው (ከጠፋ ወይም ጉዳት ከደረሰበት የማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታዎን መክፈት አይችሉም)።

በማለፊያ ቃል ፈንታ ቁልፍ ፋይልን መጠቀም የማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታዎን በቁሳዊ ቁልፍ እንደመክፈት ይቆጠራል። ማድረግ የሚጠበቅብዎት የፍላሽ ድራይቩን ከኮምፒውተርዎ ጋር ማገናኘት፣ ቁልፍ ፋይሉን መምረጥ ብቻ ነው። በዋና የማለፊያ ቃል ፈንታ ቁልፍ ፋይልን መጠቀም ከመረጡ የፍላሽ ድራይቩን ያገኘ ማንኛውም ሰው የማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታዎን መክፈት ስለሚችል ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ ማስቀመጥዎን ያረጋግጡ።

 

ሁለቱንም መጠቀም Anchor link

የማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታዎን ለማመስጠር በጣም አስተማማኝ መንገዱ ዋና የማለፊያ ቃልን እና ቁልፍ ፋይልን በአንድ ላይ መጠቀም ነው። በዚህ አካሄድ የማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታዎን የመፍታት ችሎታዎ በሚያውቁት (ዋና የማለፊያ ቃሎ) እና ባለዎት (ቁልፍ ፋይሎ) ላይ የተመሰረተ ነው። ስለዚህ የማለፊያ ቃልዎችዎን ለማግኘት የሚፈልግ ማንኛውም ሸረኛ አካል ሁለቱንም ማግኘት ይጠበቅበታል። (ይህ ከተባለ ዘንዳ የስጋት ሞዴሎን ያስታውሱ። የማለፊያ ቃልዎችዎን ለማጠራቀም ለሚፈልጉ የቤት ውስጥ ተጠቃሚዎች ጠንካራ ዋና የማለፊያ ቃል ብቻ መጠቀም በቂ ነው። ነገር ግን በመንግስት ደረጃ ካሉ እና ሰፊ ቀመራዊ ሃብት ባለቤት ከሆኑ ሸረኛ አካላት ራስዎን መጠበቅ የሚፈልጉ ከሆነ የደህንነትዎን ጥበቃ ከፍ ማድረግ የተሻለ ነው።)

አሁን ኪፓስኤክስ እንዴት እንደሚሰራ ስለተረዳችሁ በጥቅም ላይ ማዋልን እንጀምር!

 

ኪፓስኤክስን መጀምር Anchor link

አንዴ ኪፓስኤክስን ከጫኑ በኋላ ፕሮግራሙን ያስጀምሩት። ፕሮግራሙ ከጀመረ በኋላ ከፋይል ምናሌው ውስጥ “ኒው ዳታቤዝ” የሚለውን ይምረጡ። ዋና የማለፊያ ቃልን እንዲያስገቡ እና/ወይም ቁልፍ ፋይልን እንዲጠቀሙ የሚጠይቅ መገናኛ ብቅ ይላል። ምርጫዎን መሰረት በማድረግ ተገቢውን የማመልከቻ ሳጥን(ኖች) ይምረጡ። ያስተውሉ እያስገቡት ያለውን የማለፊያ ቃል ማየት ከፈለጉ (በነጠብጣብ ከመደበቅ ፈንታ) በቀኝ በኩል የ“አይን” ምልክት ያለበትን አዝራር ጠቅ ያድርጉ። በተጨማሪም ማንኛውንም ፋይል ለቁልፍ ፋይልነት ለምሳሌ የድመት ስዕልን መጠቀም ይችላሉ። ለቁልፍ ፋይልነት የመረጡት ፋይል መቼም እንደማይቀየር ማረጋገጥ አለብዎት። ምክኒያቱም ይዘቱ ከተቀየረ የማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታዎን ለመፍታት አይችልም። በተጨማሪም አንዳንዴ ፋይሉን በሌላ ፕሮግራም መክፈት የፋይሉን ይዘት ለመቀየር በቂ ሊሆን እንደሚችል ይወቁ። ኪፓስኤክስን ለመክፈት ብቻ ካልሆነ በስተቀር ፋይሉን አለመጠቀም አለ የሚባል ምርጥ ልምምድ ነው። (የቁልፍ ፋይሉን ቦታ ወይም ስም መቀየር የተሻለ ድህንነት ይሰጣል።)

በተሳካ ሁኔታ የማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታዎን ካስጀመሩ በኋላ ከፋይል ምናሌው ላይ “ሴቭ ዳታቤዝ” የሚለውን በመምረጥ ያስቀምጡት። (ያስተውሉ በኋላ ላይ የማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታ ፋይሉን ወደፈለጉበት ቦታ ማንቀሳቀስ ይችላሉ። ይህም በኮምፒውተርዎ ዋና ዲስክ ላይ ወደተለየ ስፍራ ወይም ወደሌላ ኮምፒውተር ሊሆን ይችላል። ወደሌላ ኮምፒውተር ካንቀሳቀሱት ኪፓስኤክስን እና በፊት የተጠቀሙትን የማለፊያ ቃል/ቁልፍ ፋይል በመጠቀም የውሂብ ጎታውን መክፈት ይችላሉ።)

 

የማለፊያ ቃሎችን ማደራጀት Anchor link

ኪፓስኤክስ የማለፊያ ቃሎችን በ“ግሩፕስ” እንዲያደራጁ ይፈቅዳል። እነኚህም ግሩፖች ወይም ቡድኖች ማህደሮች እንደ ማለት ናቸው። ከምናሌ አሞሌ ውስጥ “ግሩፕስ” የሚለው ምናሌ ውስጥ በመሄድ ወይም በኪፓስኤክስ መስኮት በግራ በኩል ካለው ንጥል መስኮት ግሩፕ የሚለው ላይ ቀኝ ጠቅ በማድረግ ቡድንን ወይም ንዑስ ቡድንን መፍጠር ወይም መሰረዝ ወይም ማረት ይችላሉ። የማለፊያ ቃሎችን በቡድን ማስቀመጥ ከአመቺ የማደራጃ መሣሪያነቱ ውጪ በኪፓስኤክስ ተግባራዊነት ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖ የለም።

 

የማለፊያ ቃሎችን ማጠራቀም/ማመንጨት/ማረት Anchor link

አዲስ የማለፊያ ቃልን ለመፍጠር ወይም አስቀድመው የፈጠሩትን የማለፊያ ቃል ለማጠራቀም የማለፊያ ቃሉን ማጠራቀም የሚፈልጉበት ቡድን ላይ ቀኝ ጠቅ ያድርጉ እና “አድ ኒው ኢንትሪ” የሚለውን ይምረጡ (ወይም ደግሞ ከምናሌ አሞሌ ላይ “ኢንትሪስ &ጂቲ; አድ ኒው ኢንትሪ” የሚለውን መምረጥ ይችላሉ)። ለመሠረታዊ የማለፊያ ቃል አጠቃቀም የሚከተለውን ያድርጉ፦

 • “ታይትል” በሚለው መስክ ላይ ይህን የማለፊያ ቃል ምዝገባ ለማስታወስ የሚረዳዎትን ገላጭ ርዕስ ያስገቡ።
 • በ“ዩዘርኔም” መስክ ላይ ከዚህ የማለፊያ ቃል ምዝገባ ጋር ተዛማጁን የተጠቃሚ ስም ያስገቡ። (የተጠቃሚ ስም ከሌለው ባዶውን ሊተውት ይችላሉ።)
 • “ፓስወርድ” በሚለው መስክ ላይ የማለፊያ ቃልዎትን ያስገቡ። አዲስ የማለፊያ ቃል እየፈጠሩ ከሆነ (ይህም ድረገጽ ላይ ሊመዘገቡ ቢሆን እና አዲስ፣ ልዩ፣ የዘፈቀደ የማለፊያ ቃል መፍጠር ቢፈልጉ) በቀኝ በኩል የሚገኘውን “ጀን” የሚለውን አዝራር ጠቅ ያድርጉ። ይህም የዘፈቀደ ማለፊያ ቃል ማመንጨት የሚያስችልዎትን የማለፊያ ቃል አመንጪ “ብቅ ባይ” መገናኛ ያመጣልዎታል። በዚህ መገናኛ ውስጥ ብዙ ምርጫዎች አሉ። ከእነዚህም ውስጥ የማለፊያ ቃሉ የትኞቹን ምልክቶች እንዲያካትት እንደሚፈልጉ እና ርዝመቱን ጭምር ይገኙበታል።
  • ያስተውሉ በዘፈቀደ የማለፊያ ቃል ካመነጩ የማለፊያ ቃሉ ምን እንደሆነ ማስታወስ (ወይም ማወቅ!) አይጠበቅብዎትም! ኪፓስኤክስ ያጠራቅምልዎታል። ስለዚህም የማለፊያ ቃሉን መጠቀም በሚያስፈልግዎ በማንኛውም ወቅት በተገቢው ፕሮግራም ላይ ቀድተው መለጠፍ ይችላሉ። ይህም የማለፊያ ቃል ካዝና ዋና አላማ ነው። የማለፊያ ቃሎቹ ምን እንደሆኑ ማወቅ ሳያስፈልግዎት የተለያዩ ረዥም እና በዘፈቀደ የተፈጠሩ የማለፊያ ቃሎችን ለእያንዳንዱ ድረገጽ እና አገልግሎት መጠቀም!
  • በዚህም ምክንያት የማለፊያ ቃሉን አገልግሎቱ የሚፈቅደውን ያህል ማርዘም እና የቻሉትን ያህል የተለያዩ ምልክቶችን መጠቀም ይችላሉ።
  • አንዴ ምርጫዎ ከተስማማዎት የማለፊያ ቃሉን ለማመንጨት በመስኮቱ የታችኛው ቀኝ የሚገኘውን “ጀነሬት” የሚለውን ጠቅ ያድርጉ እና ቀጥለው “ኦኬ”ን ጠቅ ያድርጉ። የመነጨው የዘፈቀደ የማለፊያ ቃል በቀጥታ “ፓስወርድ” እና “ሪፒት” በሚለው መስክ ላይ ገብቶ ያገኙታል። (የዘፈቀደ የማለፊያ ቃልን የማያመነጩ ከሆነ የመረጡትን የማለፊያ ቃል “ሪፒት” በሚለው መስክ ውስጥ እንደገና ማስገባት ይጠበቅብዎታል።)
 • በመጨረሻም ኦኬ የሚለውን ጠቅ ያደርጉ። የማለፊያ ቃልዎ በማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታዎ ውስጥ ይጠራቀማል። ለውጦቹ እንደተቀመጡ እርግጠኛ ለመሆን “ፋይል &ጂቲ; ሴቭ ዳታቤዝ” የሚለው ጋር ሄደው አርትዖት የተደረገበትን የማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታዎን ማስቀመጥዎን ያረጋግጡ። (በሌላ መልኩ ስህተት ከሰሩ ደግሞ ውሂብ ጎታ ፋይሉን ዘግተው እንደገና በመክፈት ሁሉንም ስህተቶች ማስወገድ ይችላሉ።)

ያጠራቀሙትን የማለፊያ ቃል መቀየር ወይም አርትዖት ማድረግ ቢያስፈልግዎት የማለፊያ ቃሉ ያለበት ቡድንን ይምረጡ እና በቀኝ በኩል ካለው ንጥል መስኮት አርዕስት ላይ ሁለቴ ጠቅ ያድርጉ። ከዛም “ኒው ኢንትሪ” መገናኛ እንደገና ብቅ ይላል።

 

መደበኛ አጠቃቀም Anchor link

በማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታዎ ያስቀመጡትን ግብዓት ጥቅም ላይ ለማዋል በግብዓቱ ላይ ቀኝ ጠቅ ያድርጉ እና “ኮፒ ዩዘርኔም ቱ ክሊፕቦርድ” ወይም “ኮፒ ፓስወርድ ቱ ክሊፕቦርድ” የሚለውን ይምረጡ እና የተጠቃሚ ስምዎን ወይም የማለፊያ ቃሎን ማስገባት ወደፈለጉበት መስኮት ወይም ድረገጽ ሄደው በተገቢው መስክ ላይ ይለጥፉት። (በግብዓቱ ላይ ቀኝ ጠቅ ከማድረግ በተጨማሪ የሚፈልጉት የግብዓት ተጠቃሚ ስም ወይም ማለፊያ ቃል ላይ ሁለቴ ጠቅ በማድረግ የተጠቃሚ ስሙን ወይም የማለፊያ ቃሉን በቀጥታ በቅንጥብ ሰሌዳው ላይ መቅዳት ይችላሉ።)

 

ስልጡን አጠቃቀም Anchor link

የቁልፍ ሰሌዳዎ ላይ ልዩ የሆነ የቁልፎች ስብስብን ሲጫኑ የተጠቃሚ ስምዎን እና የማለፊያ ቃልዎን በሌላ ፕሮግራሞች ውስጥ ማስገባቱ የኪይፓስኤክስ ከብዙ በጣም ጠቃሚ ገጽታዎች መካከል አንዱ ነው። ያስተውሉ ይህ ገጽታ በሊኒክስ የሚሰሩ ኮምፒውተሮች ብቻ ላይ የሚገኝ ቢሆንም እንደ ኪፓስ (ኪፓስኤክስ የተመሰረተው በእዚህ ላይ ነው) ያሉ ሌሎች የማለፊያ ቃል ካዝናዎች ይህንን ገጽታ በሌሎች ስርዓተ ክወናዎች (ኦፕሬቲንግ ሲስተሞች) ላይ በተመሳሳይ መንገድ ይሠራሉ።

ይህንን ገጽታ ለማስቻል የሚከተለውን ያድርጉ

1. ሉላዊ የማፍጠኛ ቁልፍዎን ይምረጡ። ከ“ኤክስትራስ” ምናሌ “ሴቲንግስ” የሚለውን ከመረጡ በኋላ “አድቫንስድ” የሚለውን በግራ በኩል ካለው ንጥል መስኮት ላይ ይምረጡ። “ግሎባል አውቶ ታይፕ ሾርትከት” የሚለው መስክ ውስጥ ጠቅ ያድርጉ እና ለመጠቀም የሚፈልጉትን የአቋራጭ ቁልፍ ስብስብ ይጫኑ። (ለምሳሌ Ctrl፣ Alt እና Shiftን ተጭነው ይቆዩ እና ቀጥለው “p”ን ይጫኑ። የሚፈልጉትን የቁልፍ ጥምረት መጠቀም ይችላሉ ነገር ግን ሌሎች መተግበሪያዎች ከሚጠቀሟቸው የማፍጠኛ ቁልፎች ጋር የማይጋጩ መኾኑን ማረጋገጥ አለብዎት። ስለዚህ እንደ Ctrl+X ወይም Alt+F4 ካሉ ጥምረቶች ለመራቅ ይሞክሩ።) ከተስማማዎት “ኦኬ” የሚለውን ጠቅ ያድርጉ።

2. ለማለፊያ ቃል የተወሰነ ራስ ተይብን ማዋቀር የማለፊያ ቃሉን ማስገባት የፈለጉበት መስኮት ክፍት እንደሆነ ያረጋግጡ። በመቀጠል ወደ ኪፓስኤክስ ይሂዱና ራስ ተይብን ማስቻል የሚፈልጉትን ግብዓት ያግኙ እና “ኒው ኢንትሪ” መገናኛውን ለመክፈት በግብዓቱ ርዕስ ላይ ሁለቴ ጠቅ ያድርጉ።

3. “ቱልስ” የሚለውን በታችኛው ግራ ክፍል ያለው አዝራር ላይ ጠቅ ያድርጉ እና “አውቶ-ታይፕ: ሴሌክት ታርጌት ዊንዶው” የሚለውን ይምረጡ። ብቅ በሚለው መገናኛ ላይ ተቆልቋይ ሳጥኑን ያስፉ እና የተጠቃሚ ስሙ እና የማለፊያ ቃሉ እንዲገባበት የሚፈልጉትን የመስኮት ርዕስ ይምረጡ። ኦኬ ላይ ጠቅ ያድርጉ እና በድጋሚ ኦኬ ላይ ጠቅ ያድርጉ።

ይሞክሩት! አሁን የተጠቃሚ ስምዎን እና የመለፊያ ቃልዎን ራስ ተይብ ለማድረግ ኪፓስኤክስ የተጠቃሚ ስምዎን/የማለፊያ ቃልዎን ራስ ተይብ እንዲያደርግልዎት የሚፈልጉበት መስኮት/ድረ ገጽ ጋር ይሂዱ። ጠቋሚው የተጠቃሚ ስሞን የሚያስገቡበት ቅጥረጹፍ ውስጥ መሆኑን ያረጋግጡ እና ከላይ ለሉላዊ የማፍጠኛ ቁልፍነት የመረጧቸውን የቁልፍ ስብስቦችን ይጫኑ። ኪፓስኤክስ ክፍት እስከሆነ ድረስ (ምንም እንኳ ያነሰ ወይም ትኩረት የሌለበት ቢሆንም) የተጠቃሚ ስምዎት እና የማለፊያ ቃልዎት በቀጥታ መግባት አለበት።

ያስተውሉ እንደ የድረ ገጹ/የመስኮቱ አወቃቀር ይህ ገጽታ መቶ በመቶ ወዲያውኑ በትክክል ላይሰራ ይችላል። (ለምሳሌ የተጠቃሚ ስሙን አስገብቶ ነገር ግን የማለፊያ ቃሉን ላያስገባ ይችላል።) ምንም እንኳ ይህ ገጽታ እንዲሠራ መላ መፈለግ እና ማበጀት ቢችሉም ለበለጠ መረጃ ይህን የኪፓስ ሰነድ እንዲመለከቱ እናሳስባለን። (በኪፓስ እና ኪፓስኤክስ መካከል አንዳንድ ልዩነቶች ቢኖሩም ይህ ገጽ ትክክለኛውን መንገድ ለመምራት በቂ ነው።)

በአጋጣሚ ለመጫን አዳጋች የሆነ የቁልፍ ስብስብን እንዲጠቀሙ እናሳስባለን። የባንክ አካውንት የማለፊያ ቁልፍዎን በስህተት የፌስቡክ ገጾ ላይ መለጠፍ አይፈልጉም!

 

ሌሎች ገጽታዎች Anchor link

በውሂብ ጎታዎ ውስጥ ያስቀመጡትን ግብዓት ለመፈለግ የመፈለጊያ ሳጥን (በዋናው የኪፓስኤክስ መስኮት ሰሪ አሞሌ ውስጥ ያለ ቅጥረጽሑፍ) ውስጥ ስለሚፈልጉት ነገር ይተይቡ እና ከቁልፍ ሰሌዳው ላይ አስገቢ ቁልፍን (enter) ይጫኑ።

በዋና መስኮት ውስጥ የሚገኘው የአምዱ ራስጌ ላይ ጠቅ በማድረግ ግብዓቶችዎን መደርደር ይችላሉ።

በተጨማሪም “ፋይል &ጂቲ; ሎክ ወርክስፔስ” የሚለውን በመምረጥ ኪፓስኤክስን “መዝጋት” ይችላሉ። ይህም ኪፓስኤክስን ክፍቱን መተው ያስችልዎታል። ነገር ግን የማለፊያ ቃል ውሂብ ጎታዎን በድጋሚ ከመጠቀምዎ በፊት ዋና የማለፊያ ቃልዎን (እና/ወይም ቁልፍ ፋይልዎን) ይጠይቅዎታል። ኪፓስኤክስን ለተወሰነ ጊዜ ካልተጠቀሙት በቀጥታ ራሱን እንዲዘጋ ማድረግ ይችላሉ። ይህም በሆነ አጋጣሚ ከኮምፒውተርዎ ከራቁ ሌላ ሰው የማለፊያ ቃልዎትን እንዳያገኝ ይከላከላል። ይህን ገጽታ ለማስቻል ከምናሌው “ኤክስትራስ &ጂቲ; ሴቲንግስ” የሚለውን ይምረጡ እና ሴኪዩሪቲ ኦፕሽንስ የሚለው ላይ ጠቅ ያድርጉ። ከዛም “ሎክ ዳታቤዝ አፍተር ኢንአክቲቪቲ ኦፍ {ነምበር} ሰከንድስ” የሚለውን ሳጥን ይምረጡ።

በኪፓስኤክስ ከተጠቃሚ ስም እና ከማለፊያ ቃል በተጨማሪ ሌሎች ነገሮችንም ማጠራቀም ይቻላሉ። ለምሳሌ የአካውንት ቁጥርዎን፣ የምርት መታወቂያ ቁጥር፣ መለያ ቁጥር ወይም የመሳሰሉትን ነገሮች የሚያጠራቅም ምዝገባን መፍጠር ይችላሉ። በ“ፓስወርድ” መስኩ ላይ የሚያስገቡት ውሂብ የማለፊያ ቃል ብቻ መሆን አለበት የሚል መስፈርት የለም። የፈለጉት ነገር ሊሆን ይችላል። በማለፊያ ቃል ፈንታ በ“ፓስወርድ” መስኩ ላይ ማስቀመጥ የፈለጉትን ነገር ያስገቡ (የተጠቃሚ ስም ከሌለው የ“ዩዘርኔም” መስኩን ባዶውን ይተውት) እና ኪፓስኤክስ ደህንነቱ በተጠበቀ እና አስተማማኝ በሆነ መንገድ ያስታውስዎታል።

ኪፓስኤክስ ለአጠቃቀም ቀላል፣ እና ጠንካራ ሶፍትዌር ስለሆነ ሁሉንም ጠቃሚ ተግባራቱን ለመማር ፕሮግራሙን እንዲያስሱ እንመክራለን።

JavaScript license information