የመስመር ላይ ቅድመ ምርመራን ማለፍ

ይህ እጅግ በጣም አጭር የኾነ የመስመር ላይ ቅድመ ምርመራ እንዴት እንደሚታለፍ የሚያሳይ መመሪያ ነው። ይሁንና መመሪያው ሙሉ የሚባል አይደለም። በጣም ጥልቀት ባለው መንገድ የመስመር ላይ ቅድመ ምርመራን ማለፍ እንዴት እንደሚቻል ለማወቅ የFLOSS ቅድመ ምርመራን ማለፍ የሚለውን መመሪያ ይመልከቱ።

የመስመር ላይ ቅድመ ምርመራ ምንድን ነው? መንግስታት፣ ኩባንያዎች፣ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪዎች ሶፍትዌርን በመጠቀም ተጠቃሚዎች የተለያዩ ድረ ገጾችን እና የኢንተርኔት አገልግሎቶችን መጎብኘት እንዳይችሉ የሚያደርግ ስርዓት ነው። የተለያዩ ድረ ገጾች፣ ወይም ጦማሮች እንዳይታዩ ማገድ ኢንተርኔትን ብሎክ ማድረግ ወይም ማጥለል ተብሎ የሚጠራው አንዱ የቅድመ ምርመራ ዓይነት ነው። የተለያየ ዓይነት የኢንተርኔት ማጥለል አለ። አንዳንድ ጊዜ ድረ ገጹ ሙሉ በሙሉ ሲታገድ፣ ሌላ ጊዜ የድረ ገጹ የተወሰነ ገጽታዎች ወይም ይዘቶች ብቻ ይታገዳል። አልፎ አልፎ ደግሞ የተወሰኑ ቃላትን የያዙ ድረ ገጾች ብቻ ተመርጠው ሊታገዱ ይችላሉ። ለምሳሌ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ፌስቡክ ሙሉ በሙሉ ወይም የተለያዩ የፌስቡክ ገጾች ሊታገዱ ይችላሉ ወይም “ኢትዮጵያውዊ ጋዜጠኛ አበበ ገላው ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ተቃወማቸው” የሚል ይዘት ያለው ማንኛውም የዩቲዩብ ቪዲዮ ወይም ድረ ገጽ ሊታገድ ይችላል። በአገራችን ኢትዮጵያ የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ የመንግስት ንብረት ከመኾኑ አንጻር እንዲሁም ተጠያቂነት በሌለው ኹኔታ የተለያዩ ድረ ገጾች በአገር ውስጥ እንዳይነበቡ ስለሚታገዱ ይህ መመሪያ እጅግ አስፈላጊ ነው።

አብዛኛውን ጊዜ በየትኛውም መንገድ የሚደረግ የኢንተርኔት ማጥለልን ወይም የይዘት እገዳን የተለያዩ የቆረጣ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም የታገደውን ይዘት ማግኘት ይቻላል። እነኚህ የኢንተርኔት ማጥለልን ማለፍ የሚችሉ ሶፍትዌሮች የሚሠሩት ድርዎ የሚጠቀምበትን መስመር እንዲቀይር ወይም የተለየ የትራፊክ መንገድን እንዲጠቀም በማድረግ የኢንተርኔት ማጥለሉን የሚያካሂደውን መሳሪያ በማለፍ ነው። በእዚህ ሂደት ግንኙነቱን የሚያደርጉበት ብልሃት አገልግሎት ውከላ ወይም በእንግሊዘኛው ፕሮክሲ ይባላል።

እዚህ ላይ ዜጎች እንዲያውቁ የሚገባው ነገር የቆረጣ ወይም የማለፊያ ሶፍትዌሮች፤ ግለኝነትን እና ደህንነትን እንደሚሰጡ ቃል የሚገቡት እና በስማቸው ላይ “ማንነት ሰዋሪ” የሚል ቃል የያዙት እንኳን፤ ተጨማሪ ደህንነት ወይም ማንነት መደበቅ እንደማይችሉ ነው። በመኾኑም የእርስዎን ማንነት ሊደብቅልዎት የሚችል ሌላ ማንነትዎን የሚደብቅ ሶፍትዌር መጠቀም ይኖርብዎታል።

የኢንተርኔት ማጥለልን ወይም ክልከላን ማለፍ የሚያስችሉ የተለያዩ መንገዶች አሉ። ከእነዚህም አንዳዶቹ ተጨማሪ የደህንነት ድርብ ከለላን የሚሰጡ ናቸው። ለእርስዎ ተገቢ የኾነው ሶፍትዌር በስጋት ሞዴልዎ ላይ የተመሠረተ ነው።

የስጋት ሞዴልዎ ምን እንደኾነ እርግጠኛ ካልኾኑ ከዚህ መጀመር ይችላሉ።

መሠረታዊ ቴክኒኮች Anchor link

HTTPS የHTTP የሚባለው የድረ ገጽ መዳሰሻ ስነስርዓት ደህንነቱ የተረጋገጠው ስሪት ነው። ይህም የተለያዩ ድረ ገጾችን ለመጎብኘት ያስችላል። አንዳንድ ጊዜ ቅድመ ምርመራ የሚያከናውነው አካል ደህንነቱ ያልተረጋገጠን ወይም HTTP የኾነን ድረ ገጽ ብቻ ሊዘጉ ይችላሉ። ይህ በሚኾንበት ወቅት የድረ ገጹን አድራሻ በHTTPS እንዲጀምር አድርጎ በመቀየር በቀላሉ ድረ ገጹን መጎብኘት ይችላሉ። ይህ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሚኾነው ያጋጠምዎት እቀባ አንዳንድ ቃላትን መሠረት በማድረግ ወይም የተወሰነ የድረ ገጽ ገጽታዎች ላይ የተደረገ እንደኾነ ብቻ ነው። HTTPS የሚባለው ስነስርዓት እቀባውን የሚጥለው አካል የድር ትራፊክዎን መከታተል እንዳይችሉ ሲያደርግ የትኞቹን ቃላትን እንደተጠቀሙ ወይም የትኛውን ነፍስ ወከፍ ድረ ገጽ እንደጎበኙ ማወቅ እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል (ይኹንና እቀባውን የሚጥለው አካል የጎበኟቸውን የሁሉንም ድረ ገጾች የጎራ ስም ማየት ይችላሉ)።

ይህን ዓይነት ቀላል ክልከላ እንደተደረገ ከጠረጠሩ በድረ ገጹ ስም በፊት ያለውን http:// የሚለውን https:// ብለው በመተካት ይሞክሩ።

በEFF የተዘጋጀውን HTTPS በሁሉም ቦታ የሚለውን ተሰኪ በመጠቀም አገልግሎቱ በሚደግፉ ድረ ገጾች ላይ HTTPSን በቀጥታ ማስቻል ይቻላል።

ሌላው የተለያዩ መሠረታዊ እቀባዎችን ወይም የመስመር ላይ ቅድመ ምርመራዎችን ማለፍ የሚያስችልዎ መንገድ ሌሎች አማራጭ የጎራ ስምን ወይም URLን በመቀያየር መጠቀም ነው። ለምሳሌ ቲዊተር የተሰኘወን ድረ ገጽ ለመጎብኘት http://twitter.com በመጠቀም ፈንታ የተንቀሳቃሽ ስልክ ብጅት የሆነውን http://m.twitter.com የሚለውን ይጠቀሙ። የመስመር ላይ እቀባ አድራጊዎች እገዳውን የሚያከናውኑት እቀባ የጣሉባቸውን ድረ ገጾች ወይም ገጾችን ዝርዝር በጥቁር መዝገብ በመመዝገብ ሲኾን በጥቁር መዝገቡ ውስጥ የሌሉ ማናቸውንም ገጾች ማግኘት ይችላሉ። የአንዳንድ ድረ ገጾች ወይም ጦማሮች በተለይም ገጻቸው እንዳይነበብ ከዚህ በፊት የታገደባቸው እገዳውን ለመከላከል ሌላ አማራጭ የዶሜን ስም ያስመዘግባሉ። ስለዚህ ድረ ገጽ ዝርዝር ውስጥ የሌሉ የአማራጭ የዶሜን ስሞችን በመጠቀም እገዳውን ማለፍ ይቻላል።

በድር ላይ የተመሰረቱ የውከላ ዘዴዎች Anchor link

ይህ በእንግሊዝኛው ዌብ ቤዝድ ፕሮክሲ በመባል ይታወቃል (ለምሳሌ http://proxy.org/)። ይህም ቀላል ኢንተርኔት ላይ የሚደረጉ እገዳዎችን ማለፍ የሚያስችል ድር ላይ የተመሠረተ የውከላ ስነስርዓት ነው። በድር ላይ የተመሠረተ ውከላን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚጠበቅብዎ የታገደውን ድረ ገጽ አድራሻ በድር ላይ በተመሠረተ የውከላ ስነስርዓት ላይ ማስገባት ሲኾን ወካዩ የታገደውን ይዘት ያሳይዎታል።

በድር ላይ የተመሠረተ ውከላ እጅግ በጣም ፈጣን እና ቀላል የኾነ የታገዱ ድረ ገጾችን የመጠቀሚያ ዘዴ ሲኾን ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ማንኛውንም ዓይነት ደህንነት የማይሰጥ እና የስጋት ሞዴልዎ የእርስዎ የኢንተርኔት ግንኙነት የሚከታተል አካል እንዳለ የሚጨምር ከኾነ ደካማ ምርጫ ነው። በተጨማሪም ሌሎች የታገዱ እና በድር ላይ ያልተመሠረቱ እንደ ፈጣን የመልዕክት አገልግሎት ያሉትን ስርዓቶችን መጠቀም አያስችልም። በመጨረሻም የስጋት ሞዴልዎን መሠረት በማድረግ ወካዩ እርስዎ መስመር ላይ የሚያደርጉት ሙሉ መረጃ ቅጂ ስለሚኖረው ግላዊነትዎ ላይ የተጋረጠ አደጋ ሊያስከትል ይችላል።

የተመሰጠረ ውከላ Anchor link

ለደህንነት ተጨማሪ ድርብ ዋስትናን የሚሰጡ እና እገዳን ማለፍ የሚያስችሉ ሚስጥራዊነትን የሚጠቀሙ ብዙ የውከላ መሳሪያዎች አሉ። ምንም እንኳ ግንኙነቱ የተደበቀ እና ሚስጥራዊ ቢኾንም የመሣሪያው አገልግሎት ሰጪዎች የእርስዎ የግል መረጃ ሊኖራቸው ይችላል። ይህ ማለት እነኚህ መሣሪያዎች ማንነትዎን ላይደብቅልዎት ይችላሉ ማለት ነው። ይህ ቢኾንም ግን መሠረታቸውን ድር ላይ ካደረጉ የውከላ መሣሪያዎች የተሻለ ዋስትና ይሰጣሉ።

ቀላሉ ዓይነት ሚስጥራዊ ድር ላይ የተመሰረተ ውከላ “https” በሚል የሚጀምር ሲኾን ይህም አብዛኛው ጊዜ ደህንነታቸው በተጠበቀ ድረ ገጾች የሚሰጥ ሚስጥራዊነትን የሚጠቀም ነው። ይኹንና የዚህ ውከላ መሣሪያ ባለቤቶች የሚልኩትን እና ከሌሎች ደህንነታቸው ከተረጋገጠ ድረ ገጾች የሚቀበሉትን ውሂብ ማየት ስለሚችሉ ጥንቃቄ መውሰድ ያስፈልግዎታል።

ሌሎች መሣሪያዎች ሁለቱንም ማለትም በድር ላይ የተመሰረቱ ውከላዎችን እና ሚስጥራዊ ውከላዎችን አደባልቀው የሚጠቀሙ ናቸው። የሚሠሩት እንደ ውከላ ሲኾኑ ነገር ግን ከታች የተዘረዘሩትን የማመስጠር አገልግሎቶችን አካትተዋል። እነኚህ ለምሳሌ አልትራሰርፍ እና ሳይፈን የሚባሉትን ያካትታል።

ሃሳባዊ የግል ኔትዎርክ ወይም VPN Anchor link

ሃሳባዊ የግል ኔትዎርክ ወይም VPN በኮምፒውተርዎ እና በሌላ ኮምፒውተር የሚደረገውን የበይነ መረብ የውሂብ ልውውጥ አመስጥሮ የሚልክ ነው። ይህ VPN የንግድ ወይም ለትርፍ ያልተቋቋመ ሃሳባዊ የግል ኔትዎርክ አገልግሎት፣ የኩባንያዎ ወይም የታማኝ ወዳጆ ሊኾን ይችላል። የVPN አገልግሎት አንዴ በትክክለኛ መንገድ ኮምፒውተርዎ ላይ ከተዋቀረ የተለያዩ ድረ ገጾችን ለመጎብኘት፣ ለኢሜል፣ ለፈጣን የመልዕክት አገልግሎት፣ IPን ተጠቅሞ ለሚደረግ የድምጽ ግንኙነት አገልግሎት (VoIP) እና ሌሎች የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ለማግኘ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። የግል ሚስጥራዊ ኔትዎርክ ወይም VPN ትራፊክዎ በሌላ በሦስተኛ ወገን እንዳይሰለል ቢከላከልም፤ የVPN አገልግሎት ሰጪው የትራፊክዎ መረጃ (የጎበኛቸውን የድረ ገጾች እና መቼ እንደጎበኛቸው የሚያሳይ) ማስቀመጥ ወይም የሚያደርጉትን የድር ዳሰሳ ሶስተኛ አካል በቀጥታ መሰለል እንዲችል ሊያደርጉ ግን ይችላሉ። የስጋት ሞዴልዎን መሠረት በማድረግ የተለያዩ የመንግስት አካላት በVPN የሚያደርጉትን ግንኙነቶች መስማታቸው ወይም የግንኙነትዎን ዝርዝር ማግኘታቸው ከባድ አደጋ ሊያስከትል የሚችል ሲኾን ለአንዳንድ የVPN ተጠቃሚዎች ግን ከሚያስከትለው ጉዳት ይልቅ VPNን ለጥቂት ጊዜ በመጠቀማቸው የሚያገኙት ጥቅም በልጦ ሊገኝ ይችላል።

ሃሳባዊ የግል ኔትዎርክን ወይም የVPN አገልግሎትን በተመለከተ ለተጨማሪ መረጃ ይህንን ጠቅ ያድርጉ። ማሳሰቢያ፦ አንዳንድ እንደ አርአያ ሊጠቀስ የሚችል የግላዊነት ፖሊሲ ያላቸው የVPN አገልግሎቶች በአታላዮች የሚመሩ ሊኾኑ ይችላሉ። የማያምኑትን የVPN አገልግሎት አይጠቀሙ።

ቶር Anchor link

በእንግሊዝኛው ቶር እየተባለ የሚጠራው ነጻ እና ክፍተ ምንጨ ኮድ የኾነው ሶፍትዌር የተሰራበት ዋናው አላማ የግለሰቦችን ማንነት ለመደበቅ ቢኾንም ቅድመ ምርመራን ለማለፍ ወይም ለመቁረጥ አግልግሎት ሊውል ይቻላል። ቶርን በሚጠቀሙበት ወቅት የሚያስተላልፉት መረጃ ደህንነት የተጠበቀ ነው ምክኒያቱም ቶር የመረጃ ትራፊክ ስርጭትዎን በእንግሊዝኛው ኦንየን ራውተርስ በሚባሉ በተለያየ ስፍራ የተበታተኑ የአገልጋይዎች ኔትወርክ (ዲስትሪቢዩትድ ኔትወርክ) እንዲተላለፍ በማድረጉ ነው። ይህ ስርዓት ግንኙነት እያደረጉት ያለው ኮምፒውተር የእርስዎን የIP አድራሻ በምንም አይነት ኹኔታ ማየት ስለማይችል እናም በእርሱ ፋንታ የግንኙነት ትራፊክዎ የተጓዘበትን የመጨረሻውን የቶር ራውተር IP አድራሻ ስለሚያይ ማንነትዎ እንዳይታወቅ ይረዳዎታል።

ቶር ማንኛውም ዓይነት ብሔራዊ የመንግሥት እቀባን ስለሚያልፍ ከተጨማሪ አማራጭ ገጽታዎች ጋር ግልጋሎት ላይ ከዋለ (ብሪጅስ እና obfsproxy) ወርቃማ ደረጃ ያለው ደህንነቱ የተጠበቀ የቅድመ ምርመራን የማለፊያ መሳሪያ ነው።በተጨማሪም በትክክል ከተዋቀረ በሀገሪቱ ኔትዎርክ ላይ ስለላን ከሚያካሂድ ማንኛውም አጥቂ የእርስዎን ማንነት ይከላከላል። ነገር ግን እጅግ በጣም ዝገምተኛ እና ለአጠቃቀም ከባድ ሊኾን ይችላል። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ እጅግ ቀርፋፋ የኔትወርክ አገልግሎት ባላቸው አገራት ቶርን መጠቀም በጣም ከባድ ነው።

ስለ ቶር አጠቃቀም የበለጠ ለማወቅ ይህንን ይጫኑ።

Last reviewed: 
2015-05-16
ይህ ገጽ ከእንግሊዘኛው ቅጂ የተተረጎመ ነው፡፡ የእንግሊዘኛው ቅጂ ምን አልባት የበለጠ የዘመነ ይሆናል፡፡
JavaScript license information